የብሪታኒያ ሠራዊትን በዘረኛነት የከሰሰው ራስ ተፈሪያን ወታደር አሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, DWIGHT PILE-GREY
ድዋይት ፓይል-ግሬይ ከብታኒያ ጦር ሠራዊት የመጀመሪያዎቹ ራስ ተፈሪያን መካከል አንዱ ነው። ጋርድስማን የተባለው ወታደራዊ ዕርከን ላይ ነበር የሚገኘው።
የአገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ላይ የዘረኛነት እና የትንኮሳ ክስ መሥርቶ አሸንፏል።
ለ16 ዓመታት የቆየበት የወታደርነት ሙያ ያከተመው አንድ ነጭ እሱ ወታደር መሆኑን እንደማያምን ከገለጸለት በኋላ መሆኑን ይናገራል።
ወታደር መሆኑን ለነጩ ወታደር ሲገልጽ “የቆዳ ቀለምህን መጠቀሚያ እያደረግክ ነው” ተብሎ መወንጀሉንም ይገልጻል።
ይህንን ተከትሎም በፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ አሸንፏል።
የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ትንኮሳን፣ መድልዎን፣ ማንገላታትን እንዲሁም ሌሎች መሰል ድርጊቶችን እንደማይታገስ አስታውቋል።
በወታደሮች መካከል አንድን ሰው በዘረኝነት ከመክሰስ ይልቅ ዘረኛ መሆን እንደሚቀል ድዋይት ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ተናግሯል።
ጉዳዩ በሠራተኞች ፍርድ ቤት የታየው ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ነበር። ብይን የተሰጠው ደግሞ በዚህ ዓመት ጥቅምት ላይ ነው።
ድዋይት ከወታደሮች መካከል ጎልቶ እንደሚወጣ ያውቅ እንደነበር ይገልጻል።
ድሬድሎክ አድርጎ ወታደር እንዲሆን የተፈቀደለት የመጀመሪያው ራስ ተፈሪያን ነው።
ወታደር የሆነው በ37 ዓመቱ ነው።
እአአ በ2005 ነው የተቀላቀለው። በወታደር ቤት ሙዚቀኛ ሆኖ ቆይቷል።
በተለያዩ ብሔራዊ መሰናዶዎች ላይም ተሳትፏል።
የወታደር ኮፍያ ውስጥ ፀጉሩን ለማስገባት መጠቅለል ይጠበቅበት ነበር።
“ስለሚገጥመኝ ነገር የተዛባ ምልከታ አልነበረኝም። ግን ተስፈኛ ነበርኩ” ይላል።
የሥራ ባልደረቦቹ ስለፀጉሩ እና አለባበሱ ይጠይቁት ነበር። ለምን ፀጉርህን እንደዚህ እንድታደርግ ተፈቀደልህ? አደንዛዥ ዕጽ ታጨሳለህ? የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይሰነዘሩለት እንደነበር ያስታውሳል።
እነዚህ አስተያየቶች “አለማወቅ” ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል።
ከእነዚህ አስተያየቶች የከፉት ግን ዘረኛ ስድቦች ነበሩ።
ሆኖም ግን ሥራውን ደስተኛ ሆኖ ከመቀጠል አላገዱትም። በዕርከን ከፍ እያለም ሄደ። ላንስ ሰርጀንት ድረስ ደርሷል።
በ2021 (እአአ) በማዕከላዊ ለንደን፣ ዌሊንግተን ወታደራዊ ሠፈር ውስጥ ከሁለት ነጭ ወታደሮች ጋር ግብግብ ገጠመው።

የፎቶው ባለመብት, DWIGHT PILE-GREY
ለሕክምና ነበር ወደቦታው የተጓዘው። ስልክ ለማነጋገር ሲወጣ መታወቂያውን ረስቶ ነበር።
የወታደር ልብሱን አላደረገም ነበር። መነጽር አድርጎም ነበር።
ስልክ አነጋግሮ ሲመለስ ነጭ ወታደር ነበር የገጠመው። ወታደር አይደለህም እንዳለውም ያስታውሳል።
“ወታደር ልሆን እንደማልችል ነው ያሰበው። ይሄ ሰውዬ መታወቂያዬን ረስቼ ወጥቼ ነው እያለ ነው ይለኝ ጀመር” ይላል።
“እንደዚህ ዓይነት ነገር የገጠመኝ በአለባበሴ ነው። በዚህ ሥራ ለዓመታት ስለቆየሁ ሰዎች ዘረኛ ሲሆኑ ይገባኛል” ሲልም ክስተቱን ያስታውሳል።
ይህ ነጭ ወታደር በዕርከን ከእሱ በታች ቢሆንም ሊያምነው አልቻለም።
ሌላ የሚያውቀው ወታደር አግኝቶ እንዲገባ ተፈቀደለት።
ወታደራዊ ልብሱን ለብሶ የእውነትም ወታደር መሆኑን ሲያሳይ ግን “የቆዳ ቀለምህን ለመጠቀም እየሞከርክ ነው” እንዳለው ያስታውሳል።

ሌላ ነጭ ወታደር በጉዳዩ ጣልቃ ከገባ በኋላ “ከተለያየ ባህል የመጡ” ወታደሮች እንዳሉ በመጥቀስ “ዘረኛ አይደለንም” እንዳለው ይናገራል።
ይህም በጣም ነበር ያስቆጣው።
የተፈጠረውን በንግግር ለመፍታት ሞክሯል።
“ሆኖም ግን የተናገሩት ነገር እንዴት ዘረኛ እንደሆነ እንኳን ሊገባቸው አልቻለም” ሲል ሁኔታውን ይገልጻል።
ይባስ ብሎ የሥነ ምግባር ቅጣት እንደሚፈጸምበት ተነገረው። ለበላይ አካል ቅሬታ ቢያቀርብም ተቀባይነት አላገኘም።
“ስለ ስሜቴ እና ደኅንነቴ ግድ የሌለው ተቋም ውስጥ መቀጠል እንደማልችል ገባኝ። እኔን መጥፎ ሰው ለማድረግ የሚሞክር ተቋም ነው” ይላል።
ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው ከዚያ በኋላ ነው።
የዘር መድልዎ እና ዘር ተኮር ትንኮሳ እንደደረሰበት ጠቅሶ ነው ክስ የመሠረተው።
መከላከያ ሚኒስቴር ስለ ግለሰብ ክሶች አስተያየት እንደማይሰጥ ቢጠቅስም ማንኛውም መድልዎ እና ትንኮሳ ተቀባይነት እንደሌለው በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
ማንኛውም ሰው ያልተገባ ድርጊትን እንዲጠቁም መከላከያው ያሳስባል።
ድዋይት እንደሚለው ግን ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ ያሉ አባላት ስለሚደርሰው መድልዎ መገንዘብ ይሳናቸዋል።
አመራር ላይ ያሉ ጥቁሮች ባሉበት መድልዎ የተሞላው ንግግር እምብዛም አይሰማም።
“ከላይ ያሉትን ሰዎች ‘ጌታዬ’ ነው የሚሏቸው። ከታች ያለነው ግን በየቀኑ ትንኮሳ ይገጥመናል” ይላል።
የሕግ ድጋፍ የሰጠችው ኤማ ኖርተን እንደምትለው፣ ዘረኛ መድልዎ ደርሶብኛል የሚል ሰው ነገሩን በማጋለጡ ለተጨማሪ መድልዎ ይጋለጣል።
“በዚህ ሂደት ብቁ ወታደር አጥተዋል” ስትልም ኤማ ትናገራለች።












