የእስራኤል እና የአሜሪካ ግንኙነት ከአሥርት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ንፋስ ገብቶታል

ፕሬዝዳንት ባይደን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ባይደን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ
ታትሟል

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሞኑ አንድ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር።

እስራኤል በራፋህ ላይ ያቀደችውን ወረራ ብትፈጽም ምን ሊፈጠር እንደሚችል ጥያቄ ሲቀርብላቸው "መሳሪያዎችን አላቀርብም" ብለው ለመመለስ አላመነቱም።

የጦር መሳሪያ ድጋፍ የአሜሪካ እና የእስራኤል ግንኙነት መሰረት ነው። ከአራት አሥርት ዓመታት በኋላ በሀለቱ አገራት መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ ንፋስ ገብቷል።

ባይደን ሲቪሎችን ከጉዳት እንዲጠብቁ እና በጋዛ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ እንዳይከሰት በመከላከል ድጋፍ እንዲያደርጉ በከየአቅጣጫው ግፊት በዝቶባቸዋል ቆይቷል።

በመጨረሻም የአሜሪካ የቅርብ ወዳጅና ስትራቴጂካዊ አጋር ለሆነችው እስራኤል የጦር መሳሪያ ላለመላክ ወስናዋል። ይህ እርምጃ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን እአአ በ1980ዎቹ ከወሰኑ በኋላ አልታየም።

ጦርነቱ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባይደን ያለምንም ጥርጥር የእስራኤል ደጋፊ በሆኑት የሪፐብሊካን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በራሳቸው እና በተከፋፈለው የዲሞክራቲክ ፓርቲ የፖለቲካ ልዩነት መሃል ላይ መገኘታቸውን የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተንታኝ እና አንጋፋ የመካከለኛው ምስራቅ የሠላም ተደራዳሪ አሮን ዴቪድ ሚለር ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ የአሜሪካን እና የእስራኤልን ግንኙነት የሚጎዳ ነገር ላለማድረግ የጣሩ መስለው ታይተዋል ብለዋል ሚለር።

እስራኤላውያን ራፋህን ለመውረር መወሰናቸው ግን የባይደንን አመለካከት ቀየረው።

ሰኞ ዕለት የእስራኤል ጦር የከተማዋ ምስራቃዊ ክፍል ላይ “ያነጣጠረ ዘመቻ” መጀመሩን ገልጸ።

የእስራኤል ታንኮችም ወደ አካባቢው ተጠግተው እንደሚገኙ ተነገረ። ነዋሪዎች የማያቋርጥ የተኩስ ድምፅ እንደሚሰማ እና አገልግሎታቸው የተገደቡ ሆስፒታሎች በቆሰሉ ሰዎች መጨናነቃቸውን ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከ100 ሺህ የሚበልጡ ሰዎች ከግጭቱ ሸሽተው የተሰደዱ ሲሆን፤ የመጠለያ፣ የምግብ እና የውሃ እጥረት አጋጥሟቸዋል ብሏል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን የተጠለሉባትን ከተማ ሙሉ በሙሉ ለመውረር መዘጋጀታቸውን ደጋግመው ተናግረዋል።

እዚያ ተደብቀው የሚገኙትን አራት የሐማስ ሻለቃዎች ለማጥፋት ትልቅ ዘመቻ እንደሚያስፈልግ እና የተኩስ አቁም ድርድር ቢደረሰም ዘመቻው እንደሚቀጥል ተናግሯል።

ኔታንያሁ ባይደንን ሲቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ኔታንያሁ ባይደንን ሲቀበሉ

ሙሉ ለሙሉ ዘመቻውን ከማድረግ ሐማስ ላይ “ያነጣጠረ ኦፕሬሽን” እንዲደረግ ዋሽንግተን ደጋግማ ጠይቃለች። ፕሬዚዳንቱ የራፋህ ወረራ “ጦርነቱን ለማርገብ እና ታጋቾችን የማስለቀቅን ዕድል ይጎዳል” ብለው እንደሚፈሩ ሚለር ተናግረዋል።

ባይደን ያገለገሉባቸውን መንግስታት በማማከር ለዓመታት ያሳለፉት የቀድሞ ባለስልጣን በበኩላቸው ፕሬዝዳንቱ ከጎረቤት አገር ግብጽ ጋር ሊፈጠር የሚችለውን ቀውስ ማስወገድ ይፈልጋሉ ብለዋል።

ተጨማሪ ወረራ ከተፈጸመ በዲሞክራቲክ ፓርቲ ውስጥ የበለጠ ቁጣ እና መከፋፈልን ሊፈጥር ይችላል የሚል ስጋት አለ ብለዋል።

“በዚህ ምክንያት መልዕክት አስተላልፏል” ብለዋል ሚለር።

ባይደን የቴሌቪዥን ቃለ መጠይቁን ከማድረጋቸው በፊት ዩናይትድ ስቴትስ ወደ እስራኤል የምትልከውን መሣሪያ "ለአፍታ ቆም አድርጋው" ነበር።

አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን "በሌሎች የጋዛ ክፍሎች እንዳየነው ከፍተኛ የጦር መሳሪያዎች ጥቅም ላይ መዋል" በከተማ አካባቢዎች ላይ ሊያስከትሉ ስለሚችሉት ተጽዕኖ ስጋት ተፈጥሯል ብለዋል።

ባለ 900 ኪሎ ግራም ቦምቦችን ተጠቅማ እስራኤል በጣም ከፍተኛ ጥፋት ልትፈጽም ትችላለች።

ሐማስን ለማጥፋት እንዲህ አይነት መሣሪያዎች አስፈላጊ ናቸው በማለት የእስራል ጦር ይከራከራል።

እስራኤል በጋዛ ጦርነት ወቅት በአንዳንድ አጋጣሚዎች አሜሪካን ያቀረበችውን የጦር መሳሪያ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ህግን ለመጣስ ተጠቅማበት ሊሆን ይችላል ሲል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አርብ ዕለት አስታውቋል።

ሪፖርቱ አክሎም በግምገማው "የተሟላ መረጃ" ስለሌለ ወታደራዊ እርዳታው ሊቀጥል ይችላል ብሏል።

በራፋህ ፍርስራሽ ውስጥ የምትራመድ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በራፋህ ፍርስራሽ ውስጥ የምትራመድ ታዳጊ

በመካከለኛው ምስራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ አዛዥ ሆነው ያገለገሉት የቀድሞ የአሜሪካ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጆ ቡቺኖ የእስራኤል ጦር ቀድማ ባገኘችው መሣሪያ ራፋህን “ምድረ በዳ” ማድረግ እንደምትችል ጠቁመዋል።

ዋሽንግተን በዓመት 3.8 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ወታደራዊ እርዳታ ለእስራኤል ትሰጣለች።

የአገሪቱ ኮንግረስ በቅርቡ ተጨማሪ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጦር እና የመከላከያ መሳሪያዎች እንድታገኝ ፈቅዷል። እስራኤል ዓለም ላይ ትልቁ የአሜሪካ የመሣሪያ ድጋፍ ተቀባይ ነች።

ኮሎኔል ቡቺኖ አክለውም በዘጊያዊነት የቆመው የመሣሪያ ድጋፍ በራፋህ ላይ ለሚሰነዘር ጥቃት ምንም ፋይዳ የለውም።

“ለዚህ ጉዳይ ለሚጨነቁ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ላሉ ሰዎች የሚጠቅም የፖለቲካ ጨዋታ ነው” ብለዋል።

በየትኛውም አቅጣጫ ቢታይም ግን የባይደን ውሳኔ የፖለቲካ አለመግባባቱን አላደበዘዘውም። ሪፐብሊካኖች በውሳኔው ጸጉራቸውን እየነጩ ነው።

የዩናይትድ ስቴትስ ሴናተር ፔት ሪኬትስ “ውሳኔው በጣም መትፎ ነው ብዬ አስባለሁ። ፕሬዚዳንቱ በእውነት ይህንን ለማድረግ ምንም ዓይነት ኃላፊነት የላቸውም" ብለዋል።

እስራኤል ያቀደችውን ጥቃት ለመፈጸም የሚያስችል አቅም እንዳላት ሲነገራቸው “ይህ ወዳጃችን እስራኤል ከአሸባሪ ድርጅት ጋር በምታደርገው ጦርነት የመደገፍ ጉዳይ ነው” ሲል መልሰዋል።

ሌላኛው የሪፐብሊካን ሴናተር ጆን ባራሶ ደግሞ እስራኤል "ሉዓላዊነቷን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ነገር በሙሉ የማድረግ" መብት እንዳላት ተናግረዋል። የባይደን እርምጃም አንድ ነገር አሳይቷል፡ “የፕሬዝዳንቱን ድክመት።”

በባይደን ፓርቲ ውስጥ ውሳኔው ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጓል።

የጋዛ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, AFP

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዲሞክራቲክ ሴናተር ክሪስ ኩንስ የፍልስጤም ሲቪሎች እንዴት እንደሚያዙ እና እንደሚጠበቁ ከፍተኛ ለውጥ ሳታደርግ እስራኤል በራፋህ ላይ ጥቃት ከሰነዘረች የወታደራዊ እርዳታ ላይ እገዳ እንዲጣል ከሁለት ወራት በፊት ጠይቀው ነበር።

“በጋዛ ያለው ግጭት… እራሳችንን እንደ ጠንካራ የእስራኤል ደጋፊዎች የምንቆጥር ነገር ግን ስለስቃይ እና ስለሰብአዊ ሁኔታዎች በጣም ለምንጨነቅ ብዙ አሳማሚ ነገሮች ነበሩት” ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኔታንያሁ ለማስቆም "ደጋግመው" ሞክረዋል ብለው ያምናሉ።

ነገር ግን ውጥረቱ ጨምሯል። ምክንያቱም የእስራኤሉ መሪ ወደ ጋዛ የሚሄደውን የሰብአዊ ዕርዳታን በሚቃወሙ እና ፍልስጤማውያንን ከዌስት ባንክ ለማባረር ከሚፈልጉ አክራሪ ፖለቲከኞች ድጋፍ ላይ ለማግኘት ነው።

"ይህ የመጀመሪያው እውነተኛ እረፍት ሊሆን ይችላል" ይላሉ ኩንስ።

ውሳኔው በሐማስ የተያዙትን ታጋቾች ለመልቀቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመድረስ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ ወቅት ላይ የመጣ ነው።

በካይሮ የተደረገው ውይይት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ያለምንም ግልጽ መፍትሔ ተበትኗል።

አንዳንድ የእስራኤል ተንታኞች ደግሞ ባይደን የወሰዱት እርምጃ የእገታ ድርድሩን እንደሚያስተጓጉል ጠቁመዋል።

የእስራኤል በራፋህ ላይ ለመሰንዘር ያሰበችው ጥቃት መገደቡ ሐማስን ይጠቅማል።

የንግግሮቹ ዝርዝሮች ጉዳዮች በአብዛኛው ግልጽ ባለመሆናቸው ይህንን ለመገምገም አስቸጋሪ ያደርገዋል። ትልቁ ያለመግባባት ምክንያት የሆነው ሐማስ ጦርነቱ እስከወዲያኛው እንዲያበቃ መጠየቁ እና እስራኤል ውድቅ ማድረጓ ነው።

በባይደን እና በኔታንያሁ መካከል ያለው ግንኙነት አምስት አስርት ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም ብዙ ውጣ ውረዶች ነበሩበት።

ሁለቱም ወጣቶች በነበሩበት ጊዜ ባይደን “ቢቢ እወድሃለሁ፣ ነገር ግን በምትለው ነገር ግን አልስማማም” ሲሉ በኔታንያሁ ጠረጴዛ ላይ ተቀምጦ በሚገኝ ፎቶ ላይ እንደፈረሙ ባይደን ተናግረዋል።

ኔታንያሁ ፕሬዚዳንቱ ለእስራኤል ላደረጉት ድጋፍ ብዙ ጊዜ ቢያወድሱም፤ ከፍልስጤማውያን ጋር በተያያዙ ዋና ዋና የፖሊሲ ጉዳዮች ግን በተደጋጋሚ መግባባት ሳይችሉ ቀርተዋል።

መስከረም 26 የደረሰው ጥቃት ሁለት ሳምንት ሳይሞላ ፈጥነው ቴል አቪቭ የደረሱት ባይደን ከአውሮፕላን እንደወረዱ ነበር ኔታንያሁ አቅፈው የታዩት።

የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት የተለያየ መልክ አለው

የፎቶው ባለመብት, EPA

ባይደን ከእስራኤሉ መሪ እና ከጦር ካቢኔያቸው ጋር ካደረጉት ስብሰባ በኋላ ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚሰጡ አረጋግጠዋል።

ማስጠንቀቂያም ግን ነበረበት፡ ከ9/11 ጥቃቶች በኋላ የሰራናቸውን ስህተቶች አትድገሙ የሚል።

“የፍልስጤም ህዝብም በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰቃየ ነው። መላው ዓለም በንጹሃን ፍልስጤማውያን ህይወት መጥፋት ያዝናል” ብለዋል።

ባይደን የጦር መሳሪያ መላክ መቆሙን ባወጁ ማግስት ኔታንያሁ የመልስ ምት ሰጡ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአሜሪካን ግፊት በመቃወም የራሳቸውን ድጋፍ ማሰባሰብ እንደሚችሉ ከተረዱ ቆይተዋል።

"ብቻችንን መቆም ካስፈለገን ብቻችንን እንቆማለን። ካስፈለገም በጥፍራችን ብቻ እንዋጋለን” ብለዋል።

የኔታንያሁ መግለጫ ለዲሞክራቲክ ሴናተር ለክሪስ ኩንስ ቀረበላቸው።

“በጥፍራቸው መዋጋት አያስፈልጋቸውም። ከእኛ ጋር ለበርካታ ዓመታት በጋራ በሠሯቸው ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎች እና ከእኛ ባገኙት መሣሪያዎች መዋጋት አለባቸው።"

“ነገር ግን የዜጎችን ጉዳት በሚቀንስ መንገድ ሊያደርጉት ይገባል” ሲል ተናግረዋል።