የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ጦሩ ፍልስጤማዊያንን ከጋዛ ለማስወጣት እንዲዘጋጅ አዘዙ

ፍልስጤማዊያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር የሀገሪቱ የጦር ኃይል "ጋዛን ለቀው መውጣት ለሚፈልጉ ነዋሪዎች" ዝግጅቱን አጠናቆ እንዲጠብቅ አሳወቁ።

ሚኒስትሩ በአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሐሳብ መሠረት ጋዛን ለዩናይትድ ስቴትስ አሳልፎ ለመስጠት እና 2.1 ሚሊዮን ፍልስጤማዊያንን በሌሎች ሀገራት ለማስፈር ዝግጅት ይሻል ብለዋል።

እስራኤል ካትዝ እንዳሉት ጋዛዊያን "የመንቀሳቀስ እና አካባቢያቸውን ለቀው የመውጣት ነፃነት" ሊኖራቸው ይገባል። አክለው እስራኤል ከሐማስ ጋር የገባችውን ጦርነት ያወገዙ ሀገራት ፍልስጠማዊያንን የመቀበል "ግዴታ" አለባቸው ብለዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገፆቻቸው "ጦርነቱ ሲቋጭ" ጋዛ ከእስራኤል ወደ ዩናይትድ ስቴትስ "ተላልፋ ትሰጣለች" ሲሉ ፅፈዋል።

ነገር ግን የፍልስጤም ፕሬዝደንት ቃል አቀባይ ይህን ዕቅድ ተቃውመውት፤ ሐሳቡ ዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥስ ነው፤ አልፎም "ፍልስጤም ለሽያጭ የምትቀርብ አይደለችም" ብሏል።

በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 7/ 2023 የሐማስ ታጣቂዎች ወደ እስራኤል ዘልቀው ገብተው ከፈፀሙት ጥቃት በኋላ ነው የእስራኤል ጦር ሐማስን ለማጥፋት በሚል ወታደራዊ እርምጃ የጀመረው።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር እንደሚለው በጦርነቱ 47 ሺህ 550 ፍልስጤማዊያን ሲገደሉ 111 ሺህ 600 ጋዛዊያን ደግሞ ቆስለዋል።

አብዛኛዎቹ የጋዛ ነዋሪዎች በጦርነት ምክንያት በተደጋጋሚ ለስደት ተጋልጠዋል። ከጋዛ ሕንፃዎች 70 በመቶ ያክሉ እንደወደሙ ይገመታል።

የጤና፣ ውሀ፣ የንፅሕና መሠረተ ልማቶች ከጥቅም ውጭ ሆነዋል። የምግብ፣ ነዳጅ፣ መድኃኒት እና መጠለያ እጥረት አለ።

የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር በኤክስ ገፃቸው በፃፉት መልዕክት የትራምፕን ሐሳብ "ትልቅ መነሳሳት" ብለው "በረዥም ጊዜ ተገንብታ ከጦርነት ነፃ እና ከሐማስ የፀዳች ጋዛ" ልትፈጠር ይገባል ብለዋል።

እስራኤል ካትዝ፤ የሀገራቸው ጦር "ማንኛውም መውጣት የሚፈልግ የጋዛ ነዋሪ ወደ ሚቀበለው ሀገር እንዲሄድ" ዕቅድ እንዲያወጣ ማዘዛቸውን አሳውቀዋል።

"ስፔን፣ አየርላንድ፣ ኖርዌይ እና ሌሎች ሀገራት እስራኤልን በሐሰት ሲወንጅሉ ነበር። እነዚህ ሀገራት ጋዛዊያንን የመቀበል ግዴታ አለባቸው። እምቢ የሚሉ ከሆነ ግን ግብዝነታቸው ይጋለጣል" ብለዋል።

ሚኒስትሩ ሐማስ ፍልስጤማዊያን ከጋዛ እንዳይወጡ እየከለከለ ነው ብለው ከወቀሱ በኋላ ጋዛዊያን "የመንቀሳቀስ እና አካባቢያቸውን ለቀው የመውጣት ነፃነት" ሊኖራቸው ይገባል ሲሉ ፅፈዋል።

ከሐማስ መሪዎቹ አንዱ ባሴም ናይም የእስራኤሉን መከላከያ ሚኒስትር "በጋዛ ያሰቡትን ባለማሳካታቸው እሱን ለመሸፋፈን እየሞከሩ ነው" ሲሉ ወቅሰው ፍልስጤማዊያን ቀያቸውን ጥለው እንደማይወጡ ተናግረዋል።

በአውሮፓውያኑ 1948 "ናቅባ" አሊያም በአረብኛ ትርጉም "ውድመት" ተብሎ በሚታወቀው ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን መኖሪያቸውን ለቀው በተሰደዱበት ወቅት ነው እስራኤል እንደ ሀገር የተመሠረተችው።

900 ሺህ የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን በዌስት ባንክ ይኖራሉ። 3.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ፍልስጤማዊያን ደግሞ በጆርዳን፣ ሶሪያ እና ሊባኖስ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግሥታት መረጃ ያሳያል።