ዝነኛው ግብ ጠባቂ ዴቪድ ዴ ሂያ ከ12 ዓመታት በኋላ ማንቸስተርን ዩናይትድን ተሰናበተ

ታትሟል

ስፔናዊው ግብ ጠባቂ ከማንቸስተር ዩናይትድ ዩናይትድ መልቀቁን አረጋገጠ።

የ32 ዓመቱ በረኛ የሰኔ ወር ሲገባደድ በማንቸስተር ዩናይትድ የሚያቆየው ኮንትራት ተጠናቆ ነበር።

“አዲስ ፈተና መጋፈጥ ግድ ይለኛል” ሲል ለ12 ዓመታት ከቆየበት ቤቱ መልቀቁን አሳውቋል።

545 ጊዜ ለዩናይትድ የተሰለፈው ዴ ሂያ በ190 ጨዋታዎች ግብ ሳይቆጠርበት የክለቡን ክብረ-ወሰን እንደጨበጠ ነው የተሰናበተው።

ዴ ሂያ ፕሮፌሽናል ሕይወቱን የጀመረው በአትሌቲኮ ማድሪድ ሲሆን በ2011 በ18.9 ሚሊዮን ፓውንድ ነው ወደ ዩናይትድ የመጣው።

የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን የኢንተር ሚላኑን ግብ ጠባቂ አንድሬ ኦናና ሊያስፈርም ይችላል እየተባለ ሳለ ነው ዴ ሂያ መልቀቁን ያረጋገጠው።

“ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ወደዚህ ክለብ ካመጡኝ በኋላ የማያልቅ ፍቅር አግኝቻለሁ” ብሏል ዴ ሂያ።

“ይህ ማሊያ ለብሼ፤ ይህን ታላቅ ክለብ በመወከሌ ትልቅ ክብር ይሰማኛል። ይህን የዓለማችን ታላቅ ክለብ መወከል በጣም ጥቂት ዕድለኞች የሚያደርጉት ነው።”

ዴ ሂያ ኮንትራቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ከክለቡ ጋር አዲስ ውል እንደተስማማ ቢነገረም ይህ ውል ድጋሚ መፈረሱ ተሰምቷል።

ዴ ሂያ በዩናይትድ ቆይታው የፕሪሚዬር ሊግ፣ ኤፍ ኤ ዋንጫ፣ አውሮፓ ሊግና ሁለት የካራባዎ ዋንጫ ማንሳት ችሏል።

ያለፈውን የውድድር ዓመት ጨምሮ ሁለት ጊዜ የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ ተብሎ ከመሸሉም በላይ አራት ጊዜ የዓመቱ የክለቡ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

ቀጣዩ የዩናይትድ ግብ ጠባቂ?

የዴ ሂያ መልቀቅ የኢንተር ሚላኑ አንድሬ ኦናና መምጣት ማረጋገጫ ሊሆን ይችላል።

ዩናይትድ ከካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ጋር ተስፋ ሰጭ የሚባል ውይይት ማድረጉ እየተዘገበ ነው።

ነገር ግን ክለቡ ያለውን በጀት ጠቅሎ ለግብ ጠባቂ ያውላል ማለት ከባድ ነው።

አሁን የኤሪክ ቴን ሃግ ተቀዳሚ ዓላማ አጥቂ ማስፈረም ነው።

ምንም እንኳ ዩናይትድ ከዴ ሂያ ጋር ሌላ ውል ለመግባት አልተስማማሁም ቢልም ምንጮች ግን ግብ ጠባቂው ውሉን ሊያራዝም ጫፍ ደርሶ ነበር ይላሉ።

አሁን ዩናይትድ ያሉት ግብ ጠባቂዎች ዲን ሄንደርሰንና ቶም ሂተን ናቸው።

ማንቸስተር ዩናይትድ በቅድመ የውድድር ዘመን ጨዋታ ረቡዕ ዕለት ኦስሎ ላይ ከሊድስ ይጫወታል።