ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ100 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲወጣ ፍርድ ቤት ፈቀደ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

የፎቶው ባለመብት, Tariku Desalegn facebook

ታትሟል

የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር በዋስ እንዲለቀቅ ፍርድ ቤት ወሰነ።

የጋዜጠኛው ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደገለጹት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና የሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው ውሳኔውን ያሳለፈው።

ችሎቱ ዛሬ ሰኞ ሰኔ 27/ 2014 ዓ.ም. ጉዳዩን በተመለከተበት ወቅት ጋዜጠኛው የዋስ መብት ተፈቅዶለት ጉዳዩን ከእስር ውጪ ሆኖ እንዲከታተል ብይን ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው ሰኔ 22/ 2014 ዓ.ም. ዐቃቤ ሕግ በጋዜጠኛው ላይ ሦስት ክሶች ማቅረቡን ተከትሎ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋስትና መብት ይፈቀድለት አይፈቀድለት በሚለው ክርክር ላይ ብይን ለመስጠት ነበር።

በባለፈው ችሎት ዐቃቤ ሕግ፣ ወታደራዊ ምስጢሮችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ሐሰተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት፣ ለአመፅ ሕዝቡን በማነሳሳት በሚል ክስ አቅርቦበታል።

በሦስቱም ክሶች ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሚሰራበት ሚዲያ ላይ በመጻፍ እነዚህን የወንጀል ተግባሮች ፈፅሟል የሚልም ወደ ሰባት የሚሆኑ የፍትሕ መፅሔቶችን በማስረጃነት መቅረባቸውንም ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

ዐቃቤ ሕግ ለክሶቹ ካቀረባቸው በፍትህ መፅሔት ላይ ከታተሙ ፅሁፎች መካከል በተደጋጋሚ የተጠቀሰው ከጄኔራል ተፈራ ማሞ ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶች እንደሆኑም ጠበቃው አስረድተዋል።

በተጨማሪም ፍትህ መፅሔት ከንግድ ፈቃድ ጋር በተገናኘ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የጻፋቸው ደብዳቤዎች፣ መከላከያ የጻፋቸው ደብዳቤዎች በማስረጃነት ተካትተዋል። በአጠቃላይም ለክሶቹ አስራ አንድ ማስረጃዎችን ዐቃቤ ሕግ አቅርቧል።

በባለፈው ችሎት ጋዜጠኛው የዋስ መብቱ ተከብሮ ጉዳዩን እንዲከታተል ጠበቃው ፍርድ ቤቱን የጠየቁ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ በምላሹ በዋስትና ሊወጡ እንደማይገባ ሦስት ምክንያቶችን በመጥቀስ ተከራክሮ ነበር።

ያቀረባቸው ምክንያቶችም ጋዜጠኛው የተከሰሰባቸው ሦስት ወንጀሎች ድምር ከባድ ቅጣት የሚያስቀጣ በመሆኑ፣ ተደራራቢ ክሶች መቅረቡ እንዲሁም ቢፈታ ሌላ ወንጀል ይፈፅማል የሚሉ ነበሩ።

ፍርድ ቤቱ በዛሬ ችሎት በዋስትና ጉዳይ ላይ የቀረበውን ክርክር አዳምጦ፣ ከአንደኛው ክስ በስተቀር የቀረቡበት ክሶቹ ተያያዥ በመሆናቸው፣ ቅጣታቸው ቀላል በመሆኑ፣ ተከሳሽ ቋሚ አድራሻ ያለው በመሆኑ፣ ቢወጣ ወንጀል ሊሰራ ይችላል የሚለው ስጋት ተነስቶም ሊሰራ የሚችለው መጻፍ በመሆኑ እና ይህም መብቱ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ትዕዛዝ መስጠቱን ጠበቃ ሔኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በዛሬው ችሎት ከተሰየሙት ሦስት ዳኞች መካከል ሁለቱ ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የዋስትና መብት የሚያስከለክል መከራከሪያ ያልተቀበሉት ሲሆን፣ አንደኛው ዳኛ ግን የዳኞቹን ውሳኔ እንደተቃወሙ ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል።

ሆኖም ሁለቱ ዳኞች ተመስገን ደሳለኝ የ100 ሺህ ብር ዋስትና አስይዞ ጉዳዩን በውጪ ሆኖ እንዲከታተል ብይን ሰጥተዋል።

በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ላይ ዐቃቤ ሕግ ባቀረው ክስ ላይ መቃወሚያ ለማቅረብም ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 11/ 2014 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱንም የተከሳሽ ጠበቃ ሔኖክ አክለዋል።  

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከ33 ቀናት በፊት ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በሁለት መኪና ተጭነው በመጡ የፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን መወሰዱ ይታወሳል።