ጦርነቱ ወደፊት ያመጣቸው የኢራን መሪዎች ከቀድሞዎቹ በላይ ለአሜሪካ ፈታኝ ይሆናሉ?

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ወር በቨርሴልስ ቤተ መንግሥት የእራት ሥነ ሥርዓት ላይ ከኢራን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ሲፈራረሙ ብዙዎች ጥያቄ አንስተዋል።
ትራምፕ ሐሳባቸውን ሳይለውጡ በፊት ፊርማቸውን እንዲያኖሩ ለማድረግ እራት ጋባዡ የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጥረት አድርገዋል።
ስምምነቱ አንድ ገጽ ከግማሽ ነው። በአውሮፓውያኑ 1919 የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሲያከትም ከተፈረመው 'የቨርሴልስ ስምምነት' ጋር ብዙዎች አነጻጽረውታል።
ስምምነቱ የአውሮፓን ሁኔታ ለውጧል። ነገር ግን ጀርመን ላይ የተጣሉት የካሳ ግዴታዎች ከ20 ዓመታት በኋላ ሌላ ዓለም አቀፍ ቀውስ አስከትለዋል።
የኢራን ስምምነትም እንዲህ ያለ ዕጣ ፈንታ ይገጥመው ይሆን?
የአሜሪካ እና ኢራን የተኩስ አቁም ስምምነት ልል መሆኑ ታይቷል። በሆርሙዝ ወሽመጥ ግጭቶች መነሳታቸው ለዚህ ማሳያ ነው።
የጦርነቱ መንስዔ መፍትሔ አለማግኘቱ አሁንም መካከለኛው ምሥራቅ ከውጥረት ላለመውጣቱ ምክንያት ይሆናል።
ጦርነቱ ሲጀመር የተገደሉትን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ ዓሊ ኻሜኒ ኢራን ቀናት በወሰደ የቀብር ሥነ ሥርዓት እየተሰናበተች ነው።
የቀደመው ሥርዓት በአዳዲስ ፊቶች ተተክቷል። አዲሱ አስተዳደር የራሱን መንገዶች የሚከተልም ይሆናል።
የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የቀድሞ የኢራን አመራሮችን ሞት አስከትሏል። እነዚህ የቀድሞ መሪዎች በአዲስ እና ጠንካራ ተገዳዳሪዎች ተተክተው ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሰላለፍ ለውጥ
በጆን ሆፕኪንስ ስኩል ኦፍ አድቫንስድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ የዓለም አቀፍ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ጥናት ባለሙያ ቫሊ ናስር "ጦርነቱ ዕውቅና ከሰጠነው በላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነው" ይላሉ።
ጦርነቱ እንደ ሌሎች ትልልቅ ጦርነቶች በመካከለኛው ምሥራቅ "የአሰላለፍ ለውጥ የሚያመጣ" መሆኑን ይናገራሉ።
ያለፈው ታኅሣሥ ኢራን በሕዝባዊ ተቃውሞ ስትናጥ ትራምፕ እና የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአስተዳደር ለውጥ እንደሚከተል ተናግረዋል።
የኢራን ምጣኔ ሃብት ለዓመታት በዘለቀ ማዕቀብ ተንኮታኩቷል። ከዚህ ቀደም ለ12 ቀናት ከእስራኤል ጋር የነበረው ግጭትም ጫና አሳድሯል።
ትራምፕ ሲፎክሩ እንደነበረው የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር እልባት አላገኘም። ጉዳዩ ለዓመታት የዲፕሎማሲ ውዝግብ መነሻ ሆኖ ቀጥሏል።
በጦርነቱ የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር ጉዳት ደርሶበታል።
10 ወይም 11 አውቶሚክ መሣሪያ ለመገንባት መዋል ይችላል የተባለው የኢራን የተከማቸ ዩራንየም የት እንዳለ በትክክል ባይታወቅም፣ በኢስፋሃን የኒውክሌር ተቋም ከምድር በታች እንደሚገኝ ይታመናል።
ኢራን 'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' የምትላቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አጋሮቿ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
የኢራን የቅርብ ወዳጅ ባሽር አል-አሳድ ከሶሪያ መሪነት ተወግደዋል። በሊባኖስ የሄዝቦላህ መሪዎች በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጋዛ ሰርጥ ሐማስ ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበታል። እስራኤል በሐማስ በጥቅምት 2023 ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹኃንን ገድላለች።
በጋዛ ጦርነት ወቅት የየመን ሁቲ አማጺያን በእስራኤል ላይ ሚሳዔል ተኩሰዋል፤ በቀይ ባሕር ላይ መርከቦችን አጥቅተዋል። እስራኤል፣ አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደምም በአጸፋው በቡድኑ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል።
ኢራን በአጋሮቿ ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ ውስጣዊ መዳከምም እንደደረሰባት ሲነገር ቆይቷል።
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው፤ ትራምፕ የደረሷቸው በርካታ የደኅንነት መረጃዎች ኢራን ከ1979 አብዮት በባሰ መዳከሟን ያሳያሉ።
ኢራን አሜሪካ እና እስራኤልን ተቋቁማ ትዋጋለች የሚለው ሩቅ ሐሳብ ይመስል ነበር። ነገር ግን እውን ሆኗል።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አሁንም ባለበት ይገኛል። በዓለም ቁልፍ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥ ዘግቶ የዓለምን ምጣኔ ሃብት የሚፈታተን ሆኗል።

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images
ቴህራን ምን አገኘች?
ትራምፕ በኢራን የአገዛዝ ለውጥ አምጥተናል ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ። ተንታኙ ቫሊ ናስር በዚህ አይስማሙም። እንዲያውም ተጠቃዋሚ ኢራን ናት ብለው ያምናሉ።
"አዲስ ትውልድ ተተክቷል። ግልጽ አጀንዳ አላቸው። ጦርነቱን እንደተቋቋሙት ሁሉ በሰላም ውስጥም መቀጠል ይችላሉ።"
ዋሽንግተን የቀድሞውን አስተዳደር "ዘመን ያለፈባቸው የአንድ ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኞች" አድርጋ ትገልጻለች።
ሆኖም ግን ከአብዮት በኋላ የመጡት መሪዎች አገሪቱን ለመጠበቅ ከቀደመው አስተዳደር በላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን ቫሊ ያስረዳሉ።
የኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ ከአባታቸው በ30 ዓመት የሚያንሱ ሲሆን፣ አሁን 56 ዓመታቸው ነው።
የቀድሞው ጠቅላይ መሪ በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ሲገደሉ በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንዳልነበሩ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤሽኪያን 71 ዓመታቸው ነው። የ1979 የኢራን አብዮት ትውልድ አሁን ላይ የለም።
ከአሜሪካ ጋር በተካሄደው ድርድር ቁልፍ ቦታ ያላቸው የኢራን ፓርላማ አፈ ጉባዔ መሐመድ ባጋር ጋባሊፍ እና የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና መሪ አሕመድ ቫሄዲ በ60ዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ።
እንደ ጠቅላይ መሪው ሁሉ ፖለቲከኞቹ ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ቅርብ ትስስር አላቸው።
ለንደን በሚገኘው የቻታም ሐውስ የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሰሜን አፍሪካ ዳይሬክተር ሳናም ቫኪል "የአብዮቱ ልጆች ናቸው" ብለው ይገልጿቸዋል።
"የ86 ዓመት ሰው የእስላሚክ ሪፐብሊኳ ጠባቂ ሆኖ አይቀጥልም። የአብዮቱ ሥርዓት የእጅ ፍሬን የምንለው ዓሊ ኻሜኒን ነበር" ይላሉ።
ኻሜኒ ለረዥም ጊዜ "ጦርነትም ሰላምም የሌለበት" ፖሊሲ ማራመዳቸው ይነገራል። ተከታዮቻቸው ግን በድፍረት የመካከለኛው ምሥራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈሮች ላይ ጥቃት ከፍተዋል።
ጦርነቱን ለማቆም ወደ ድርድር ጠረጴዛው ሲሄዱም ኢራንን የሚያሳፍሩ ነጥቦች ይዘው አልነበረም።
"ከቀደመው ትውልድ በተለየ ጦርነት ውስጥ ለመግባት ፈቃደኛ ናቸው" ይላሉ ሳናም።
በ2020 የኢራን አብዮታዊ ዘብ ኮማንደር ቃሲም ሱሌይማኒ በትራምፕ ትዕዛዝ ሲገደሉ ቴህራን የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ቀድማ አስታውቃ 12 ባለስቲክ ሚሳዔሎችን ወደ አሜሪካ ጦር ሰፈሮች እና ወደ ኢራቅ ተኩሳለች። በጥቃቱ የአሜሪካ ወታደሮች አልተገደሉም።
ዘንድሮ አሜሪካ እና እስራኤል የለየለት ጦርነት ሲከፍቱ ኢራን በርካታ ድሮን እና ሚሳዔል ተኩሳለች። ጥቃቱ በኳታር የሚገኘው አል-ኡዴይድ የአየር ኃይል ሰፈር እና በባህሬን የሚገኘው አምስተኛው የባሕር ኃይል ምድብ የጦር ሰፈርን ያካትታል።
በኩዌት ስድስት የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ በአጠቃላይ ውጊያው ሌሎች ተጨማሪ ወታደሮች ተጎድተዋል።
ኢራን በባሕረ ሰላጤው የሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮችን ለማጥቃት ወደ ኋላ እንደማትል እና የሆርሙዝ ወሽመጥን ለመዝጋት መወሰኗ ዋይት ሐውስን አስገርሟል።
ኢራንን በወታደራዊ መዋቅር እና በባሕረ ሰላጤው አገራት ድጋፍ መቆጣጠር እንደምትችል አሜሪካ ታምን ነበር።
ይሄ አካሄድ እንደማይሠራ ኢራን በግልጽ አሳይታለች።
በኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ የኢራን ፕሮጀክት ዳይሬክተር ዓሊ ቫዬዝ "አብዛኞቹ አገራት የአሜሪካ ጦር ሰፈር በግዛታቸው መገኘቱ ከለላ እንደሚሰጣቸው ያምኑ ነበር። ነገር ግን ዒላማ እንዲሆኑ ምክንያት ሆኗል" ይላሉ።
አሜሪካ የምትሰጠው የደኅንነት ከለላ ላይ የባሕረ ሰላጤው አገራት ጥያቄ ማንሳት መጀመራቸውን ያስረዳሉ።
የባሕረ ሰላጤው አገራት ከኢራን ጋር እርቅ ለማውረድ እየሞከሩ ነው።
በ2023 ሳዑዲ አረቢያ ከኢራን ጋር ወዳጅነቷን ማደሷን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል አንድ ዲፕሎማት ጠቅሶ ዘግቧል።
ሳዑዲ ኢራንን ከቀጣናው ጎረቤቶቿ ጋር ለማቀራረብ ጉባዔ ስታሰናዳም ነበር።
የቀጣናው አገራት በጦርነቱ መካከል ቢወድቁም ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማበላሸት እንደማይፈልጉ ተንታኙ ይናገራሉ።
"ደኅንነትን በተመለከተ ሙሉ በሙሉ አሜሪካ ላይ የተንተራሱ ስለሆነ ሙሉ በሙሉ ግንኙነት ማቋረጥ ይከብዳል። ሌላ የተሻለ አማራጭም የላቸውም" ይላሉ።
ከዚህ ቀደም በጠላትነት ይተያዩ የነበሩ ወገኖች አዲስ ዓይነት ግንኙነት መመሥረት የሚያስቡበት ወቅት እንደሆነ ያስረዳሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አዲሱ አመራር
በኢራን ሕዝባዊ ተቃውሞ ሲነሳ ትራምፕ "እርዳታ እየላክን ነው" ማለታቸው ይታወሳል። ከዚያም ኢራን ላይ ጥቃት ከፈቱ።
"ስንጨርስ መንግሥታችሁን ገንቡ፤ የእናንተው ነው" ሲሉ ለኢራናውያን ጥሪ አስተላልፈው ነበር።
ይሄ ቃል የሚተገበር አይመስልም። አዲስ ትውልድ በኢራን ቢመጣም ለሕዝቡ ነጻነት እና ዕድገት ተስፋ የሰጠ አይደለም።
አቡ ዳቢ የሚገኙት የቻታም ሐውስ ቲንክ ታንክ ባለሙያ አኒሽ ባሳሪ ታባሪዚ የሚለወጥ ነገር ይኖራል ብለው አያምኑም።
ከመንግሥት ተቋማት ውጭ ሒጃብ መልበስን አስገዳጅ የሚያደርግ ሕግ አለመተግበሩ፣ በቴህራን ሬስቶራንቶች አልኮል መጠጥ መቅረቡ እና ሌሎችም መሰል ውሳኔዎች ቀድሞ እንደ ነውር የሚቆጠሩ ድርጊቶች ላይ ያለው ምልከታ መለወጡን ያሳያሉ።
ቫሊ እንደሚሉት ይሄ ለውጥ የመጣው "አስገዳጅ ሁኔታ" ስላለ ነው።
ኢራን ከወራት በፊት በሕዝባዊ ተቃውሞ መናጧን ተከትሎ የቴህራን መንግሥት ቢያንስ አገራዊ ሉዓላዊነትን መጠበቅ እንደሚችል አሳይቷል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለኢራናውያን ጦርነቱ ግራ አጋቢ ሆኗል። በአንድ በኩል የቴህራን መንግሥት ጭካኔ የተሞላቸው ድርጊቶች ሲፈጽም ቆይቷል። በሌላ በኩል ደግሞ ኢራን በአገራቸው ላይ ያዘነበችው ቦምብ ንጹኃንን የገደለ፣ መሠረተ ልማት ያወደመም ነው።
በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀን በሚናብ በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት፤ ትክክለኛው ጠላት ማነው? የሚል ጥያቄ አጭሯል።
አሜሪካ ኢራናውያንን ነጻ ለማውጣት ቃል ገብታ አገሪቷን ማፍረስ ጀምራለች።
የአሜሪካ እና እስራኤልን አቅም ተቋቁሞ የኢራን መንግሥት የጠፋውን ስሙን ማደስ ይችላል?
ተንታኙ እንደሚሉት ነገሩ "የቻይናው ማኦ ንቅናቄ" ዓይነት ነው።
አዲሱ ሥርዓት አዲስ ማኅበራዊ መዋቅር እንደሚያስፈልገው ይረዳል። ማሳካት ይችላል ወይ? የሚለው ግን አጠያያቂ መሆኑን ይገልጻሉ።
የኢራን ልሂቃን በሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት አጋሮቻቸውን አጥተዋል። አሁን ላይ አገሪቱ በእስላማዊ አብዮታዊ ዘቡ ውሳኔ ሰጭነት ትመራለች።
ልሂቃን የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ በመወሰን ረገድ ተሰሚነት እንዳላቸው አይሰማቸውም።
የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ የዋሽንግተን እና ቴህራንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት "ከሥር ከመሠረቱ የተለወጠ ነው" ሲሉ ገልጸውታል።
ኢራን ማዕቀቦቿ ሲነሱላት የኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ ገደብ ለማድረግ በመስማማት ምጣኔ ሃብቷን ስታሻሽል፤ የቴህራን መንግሥት ገጽታውን ይገነባል።
የመግባቢያ ሰነዱ ከተፈረመ በኋላ ኢራን የተወሰኑ ማዕቀቦች ተነስተውላት ተጠቃሚ ሆናለች። ለ60 ቀናት ድፍድፍ ነዳጅ ኤክስፖርት ማድረግም ትችላለች።
በ60 ቀናት ውስጥ በሚኖር ድርድር ሌሎችም ጥቅሞች ልታገኝ ትችላለች። በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የኢራን ሃብት ላይ የተጣለው ዕገዳ መነሳት ይጠቀሳል።
የመጨረሻው የስምምነት አካል የሁሉም ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች መነሳት ይሆናል።
በስምምነቱ መሠረት "ለመልሶ ግንባታ እና ዕድገት የሚውል" 300 ቢሊዮን ዶላር መመደቡ ተገልጿል።
እነዚህ ጥቅማ ጥቅሞች ለኢራን አዲስ አስተዳደር ድርድር የማድረግ አቅም ይሰጣሉ።
"ስምምነት ላይ ሳይደረስ እየተጓተተ ቆይቶ ትራምፕ ተሰላችተው ወደ ሦስተኛ ዙር ጥቃት ሊመለሱ የሚችሉበት ዕድል በቀጣናው ያንዣብባል" ሲሉ አኒሽ ያስረዳሉ።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ተንታኞች ለወደፊት ምን እንደሚከሰት እርግጠኛ አይደሉም።
በኢራን እና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንዲሁም በአሜሪካ መካከል ያለው ለዘመናት የዘለቀው አለመተማመን ነገሮችን በጥርጣሬ እንዲታዩ ምክንያት ነው።
የኢራን የኒውክሌር መርሃ ግብር፣ የሆርሙዝ ወሽመጥ አስተዳደር፣ የሊባኖስ ጦርነት እና የፖለቲከኞች አቋም ጥያቄ የሚያስነሱ ናቸው።
ባለፉት ስድስት ወራት ቀጣናው ተለውጧል። የተሻለ ነገር እስከሚመጣ ግን ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።















