በዓለም ዋንጫ ለአሜሪካው አጥቂ የተሰጠው ቀይ ካርድ በትራምፕ ጣልቃ ገብነት ተቀለበሰ

አጥቂው ፎላሪን ባልገን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አጥቂው ፎላሪን ባልገን አንዷ የዓለም ዋንጫ አዘጋጅ ለሆነችው አሜሪካ ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

አሜሪካ ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ከቦሲኒያ ሄርዜጎቪኒያ ጋር ባደረገችው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ላይ በተቃራኒው ቡድን ላይ በሰራው ጥፋት ለአሜሪካው አጥቂ ፎላሪን ባልገን የተሰጠው ቀይ ካርድ እንዲታገድ ተደረገ።

የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) አጥቂው በቀጣዩ የአገሪቱ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ እንዳይሳተፍ የሚያግደው ውሳኔን የሻረው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ከገቡ በኋላ ነው።

በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሦስት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው የ25 ዓመቱ አጥቂ፤ ቀይ ካርድ የተሰጠው የቦሲኒያ ሄርዜጎቪኒያ አጥቂ ታሪክ ሙሃሬሞቪች ላይ በሰራው ጥፋት ነበር።

ፊፋ ከዚህ በኋላ በሰጠው ትዕዛዝ፤ ቀይ ለካርድ ያገኙ ተጫዋቾች በቀጣዩ ጨዋታ እንዳይሳተፉ የሚያደርገው አሰራር ለአንድ ዓመት እንዲታገድ መወሰኑን አስታውቋል።

ፊፋ ቅጣቶች እንዲታገዱ ማድረግ የሚያስችል ሕግ መኖሩን ከመጠቀስ ውጪ ለምን አሁን ይህንን ውሳኔ እንዳስተላለፈ አላብራራም።

በመግለጫ፤ "በፊፋ የስነ ምግባር ደንብ አንቀጽ 27 መሠረት ከጨዋታ የማገድ ውሳኔ ተፈጻሚነት ለአንድ ዓመት ለሚቆይ ጊዜ ታግዷል" ብሏል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ ፊካ ይህንን "ታላቅ ኢፍትሐዊነት ስለቀለበሰ" አመስግነዋል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ኒውስ፤ አጥቂው ወደ ጨዋታ እንዲመለስ የሚያስችል ውሳኔ የተላለፈው ትራምፕ ሐሙስ ዕለት ለፊፋው ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋነቲኖ ከደወሉላቸው በኋላ ነው።

የቤልጂየም እግር ኳስ ማህበር በፊፋ ውሳኔ "እጅግ መደነቁን" ገልጾ፤ "ያሉትን አማራጮች በሙሉ እንደሚመለከት" አስታውቋል።

የትራምፕ እና የፊፋው ፕሬዝዳንት በነበራቸው አጭር ንግግር ስለ እገዳው እንዳወሩ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ኢንፋንቲኖ፤ የፊፋ የስነ ምግባር ኮሚቴ ጉዳዩን እንደሚመለከተው ለትራምፕ መናገራቸውንም ምንጮቹ ገልጸዋል።

ይህ ውሳኔ እስካሁን ድረስ ተጫዋቾች በቀጣዩ ጨዋታ እንዳይሳተፉ ሲያደርግ የነበረውን የቀይ ካርድ አሰራርን ጥያቄ ውስጥ አስገብቶታል።

በዓለም ዋንጫ ታሪክ 189 ጊዜ ቀይ ካርድ የተሰጠ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ቀጣዩን ጨዋታ ያለመሳተፍ እገዳ ተፈጻሚ ያልሆነው የአሁኑን ጨምሮ ሁለት ተጫዋቾች ላይ ብቻ ነው።

ሌላኛው ተመሳሳይ ውሳኔ የተላለፈው በአውሮፓውያኑ 1962 ነው። የብራዚሉ ጋሪንቻ ከቺሊ ጋር በነበረ ጨዋታ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ በቀይ ካርድ ቢወጣም፤ ከቼክስሎቫኪያ ጋር በተደረገው የፍጻሜ ግጥሚያ ተሳትፏል።

በዚያ ወቅት የነበረው አሰራር ቀይ ካርድ ያገኘ ተጫዋች በቀጥታ ቀጣዩን ጨዋታ እንዳይሳተፍ የሚያደርግ አልነበረም። ይህንን የሚወስነው የቀሚርብለትን ማስረጃ የሚመለከተው ኮሚቴ ነበር።

ይሁን እንጂ የ1962ቱም የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ነበረበት የሚል ክስ ይቀርብበታል።