ቀጥታ, የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

የቀድሞው ኢራን አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም፤ ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል። እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ያለው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሽኝት

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥን

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥን

    ባለፈው ሳምንት መጨረሻ የተጀመረው እና በቀጣይ ቀናትም የሚካሄደው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት በመቶ ሺህዎች እየታደሙበት ቀጥሏል።

    ኻሜኒ ከአብዮታዊዋ እስላማዊት ሪፐብሊክ ኢራን መሪነታቸው በተጨማሪ በሺዓ እስልምና እምነት ተከታዮች ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው መሪ ነበሩ።

    የቀድሞው መሪ የስንብት ሥነ ሥርዓት ከኢራን በተጨማሪ በኢራቅ ውስጥ የሚከናወን ሲሆን፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደማሉ ተብሏል።

    አስካሁን በኢራን ውስጥ የተካሄደውን ሥነ ሥርዓት የሚያሳዩ የተወሰኑ ምሥሎች እነሆ...

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና
    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን ሳጥንን የያዘው መኪና

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመሰናበት አደባባይ የወጡ ሰዎች የትራምፕን ምሥል ይዘው

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ለመሰናበት አደባባይ የወጡ ሰዎች የትራምፕን ምሥል ይዘው
    አደባባይ የወጡ ሐዘንተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን ባለሥልጣናት ለቀናት በሚካሄደው የስንብት ሥነ ሥርዓት ላይ በሚሊዮኖች እንደሚገኙ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል
    የአያቶላ ምሥል ያለበት ተሽከርካሪ እና ለስንብት አደባባይ የወጡ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

  2. ኢራን ለአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ "ፍትሕ እንደምትፈልግ" የጦር አዛዧ ተናገሩ

    ከኻሜኒ ትልቅ ፎቶ ጎን የቆመ የታጠቀ ወታደር

    የኢራን የቀድሞ ጠቅላይ መሪ የሆኑት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ባለበት በአሁኑ ጊዜ፤ አገሪቱ ለግድያው ፍትሕ እና ተጠያቂነትን ለማግኘት ጥረቷን እንደምትቀጥል የኢራን ሠራዊት አዛዥ ሜጀር ጄነራል አሚር ሐታሚ ተናገሩ።

    “ወንጀሉን የፈጸሙት ወገኖች የኢራን ሕዝብ እንባ፣ ሁላችንም ፍትሕ መጠየቃችንን ፈጽሞ እንደማናቋርጥ ሊያውቁ ይገባል” በማለት የጦር አዛዡ መናገራቸውን የኢራን ዜና ወኪል ኢርና ዘግቧል።

    ጨምረውም “ውጤት አስክናገኝ ድረስ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ ለማድረግ ውሳኔያችን ግልጽ ነው። ጥቃት ፈጻሚዎቹን እንዲሁ አንተዋቸውም” በማለት በአሜሪካ እና በእስራኤል ጥቃት የተገደሉት የጠቅላይ መሪው ደም በከንቱ ፈስሶ እንደማይቀር አመልክተዋል።

    ሟቹ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ለክብር፣ ለነጻነት እና ለብሔራዊ ኩራት ፈር ቀዳጅ መሆናቸውን የጠቀሱት ጄነራሉ፤ የአገሪቱ ጦር ኃይሎች “ያለምንም ማወላወል በቆራጥነት እና በጀግንነት” የአዲሱን እስላማዊ አብዮታዊት ኢራን ጠቅላይ መሪ እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሞጅታባ ኻሜኒ አመራርን እንደሚከተል ገልጸዋል።

    ጄነራሉ አዲሱን መሪ ባገኙበት ጊዜ “የኢራን ሕዝብ እና መንግሥት ወንጀሉን የፈጸሙት እንዲሁ እንደማይተዋቸው ነግሬያቸዋለሁ” በማለት ለሞጅታባ ኻሜኒ የገቡትን ቃል አስታውሰዋል።

  3. በአያቶላህ አሊ ኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሚታየው ቀይ ባንዲራ ምንድን ነው?

    ኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቀይ ባንዲራ የያዙ ሰዎች

    የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

    ለቀናት በሚዘልቀው የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ የስንብት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ እየተገኘ ሲሆን በዚህ ሥነ ሥርዓት ላይም ከኢራን ባንዲራ ይልቅ ሐዘንተኞቹ ቀይ ባንዲራ ይዘው በስፋት ይታያሉ።

    ሐዘንተኞቹ በጠቅላይ መሪው የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ቀይ ቀለም ያለው ሰንደቅ ዓላማ ወይም ረጅም ባነር መያዛቸው በሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ቀዩ ባንዲራ ያለውን መልዕክት ለማስተላለፍ ነው። ይህም የሟቹን መሪ ደም መበቀል አስፈላጊ መሆኑን ለማመልከት ነው።

    በተጨማሪም ከሰንደቅ ዓላማ ጋር ጽሁፍ የሰፈረባቸው ቀይ ጨርቆች በስፋት የሚታዩ ሲሆን ጽሁፉ ለኻሜኒን ግድያ በቀል ጥሪ የሚያርቡ ናቸው።

    በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታዩት ቀይ ባንዲራዎች ሰማዕትነትን፣ ለንጹኃን ግድያ ፍትሕ አለማግኘትን፣ እንዲሁም ለበቀል ሃይማኖታዊ ቃል መግባትን ያመለክታል። ይህ ቀይ ባንዲራ በአጥቂዎች ላይ የበቀል አጸፋ ሲመለስ ወይም በፍርድ ፍትሕ አስኪገኝ ድረስ እየተውለበለበ ይቆያል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በየካቲት መጨረሻ በኢራን ላይ ጦርነት በከፈቱ ጊዜ በመጀመሪያው ቀን በፈጸሙት ጥቃት ጠቅላይ መሪው አሊ ኻሜኒ፣ የቤተሰብ አባሎቻቸው እንዲሁም የአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ መሪዎች መገደላቸው ይታወሳል።

    ኢራንን ወደ 40 ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በጠቅላይ መሪነት ያስተዳደሩት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከአገሪቱ ባሻገር በሌሎች አገራት ውስጥ በሚገኙ የሺዓ ሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ ተደማጭነት ነበራቸው።

    ከቅዳሜ ጀምሮ አስከ ሐሙስ ድረስ የሚቆየው የኻሜኒ የቀብር ሥነ ሥርዓት ከኢራን ባሻገር በጎረቤት አገር ኢራቅ ውስጥም ይካሄዳል። የጠቅላይ መሪው አስከሬን ወደ ኢራን የሚወሰድ መሆኑም ተነግሯል።

  4. የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት በታደሙበት የቀድሞው መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ መሪው ሳይገኙ ቀሩ

    ትራምፕ ይገደሉ የሚል መፈክር የያዘች እና ሌሎች ሐዘንተኞች

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የቀድሞው የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ የቀብር ሥነ ስርዓት ላይ በርካታ የአገሪቱ አመራሮችን ጨምሮ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቢገኙም ጠቅላይ መሪው ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸው ሽኝት ላይ ሳይታዩ ቀርተዋል።

    እሁድ ዕለት በተካሄደው የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ የቀድሞው ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ሦስት ልጆች መስዑድ፣ ሙስጠፋ እና መይሰም ከፕሬዝዳንት መስዑድ ፔዜሽኪያን እና ከእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ መሪ አህመድ ቫሂዲ ጋር ተገኝተዋል።

    መጋቢት ላይ ወደ ሥልጣን ከመጡ አንስቶ ለሕዝብ ያልታዩት ሞጅታባ ኻሜኒን የጤና ሁኔታ በተመለከተ የተለያዩ መረጃዎች ይናፈሳሉ። አባታቸውን በገደለው የአየር ጥቃት እርሳቸውም እንደተጎዱ ይነገራል።

    የቀድሞው ጠቅላይ መሪ ከአውሮፓውያኑ 1989 ጀምሮ እስከሞቱበት የካቲት ወር ድረስ እስላማዊቷን ሪፐብሊክ መርተዋል።

    አርብ ዕለት የተጀመረው የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ይፋዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት በዚህ ሳምንትም በተለያዩ የኢራን እና ኢራቅ አካባቢዎች መካሄድ ይቀጥላል።

    የኢራን ባለሥልጣናት “የክፍለ ዘመኑ የቀብር ሥነ ሥርዓት” ሲሉ በገለጹት በዚህ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ከ12 እስከ 20 ሚሊዮን ሰዎች ይገኛሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

    በአሁኑ ሰዓት የኻሜኒ አስከሬን ቴህራን ውስጥ በሚገኘው ግዙፉ መስጊድ ግራንድ ሞሳላ ውስጥ ተቀምጧል።

    እሁድ ዕለት በመላው ኢራን ክብረ በዓል ሆኖ የታወጀ ሲሆን አስከሬኑ ከመስጊዱ እንደሚወጣ እና ዛሬ ሰኞ ሰልፍ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

    የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በጥንቃቄ የተሰናዳ ነው። በሥነ ሥርዓቶቹ ላይ የሞጅታባ ኻሜኒ አለመገኘት የተስተዋለው እስራኤል ልትገድላቸው ትፈልግ ይሆናል የሚል ስጋት ባደረበት በዚህ ወቅት ነው።

    ተፋላሚዎቹ አገራት በገቡበት ጠንካራ ያልሆነው ተኩስ አቁም ምክንያት ጦርነቱ ጋብ ብሎ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረገው ንግግር ቀጥሏል።

    ይሁን እንጂ አሜሪካም ሆነ ኢራን ወታደራዊ እርምጃ ውስጥ በድጋሚ ለመግባት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

    ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ እስከሚጠናቀቅ ከኢራን ጋር የሚደረገው ንግግር እንዲቆም መደረጉን ለአሜሪካው የዜና ምንጭ አክሲዮስ ተናግረዋል።

    አሜሪካ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚታደሙትን የኢራን ከፍተኛ አመራሮች “በአንድ ጥይት” ልትገድላቸው እንደምትችልም መናገራቸውን አክሲዮስ አስነብቧል። ። ነገር ግን "ይህንን አናደርግም፤ ምክንያቱም ከዚያ የምንደራደረው ሰው አይኖርም" ብለዋል።

    ትራምፕ ሕዝቡ የቀድሞውን ጠቅላይ መሪ ይጠላቸዋል ብለው ያስቡ እንደነበር ገልጸው፤ የተወሰኑ ኢራናውያን ሲያለቅሱ በመመልከታቸው እንደተገረሙ ተናግረዋል።

    በቴህራን በተደረገው ሽኝት ላይ ታዳሚዎች 'ሞት ለትራምፕ' ሲሉ እንደነበር እንዲሁም ሞሐማድ ረሱሊ የተባሉ ገጣሚ ከጸሎት ሥነ ሥርዓት በፊት “ትራምፕን መግደል የእኛ ኃላፊነት ነው” የሚል ግጥም ማቅረባቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ እና ዘ ጋርዲያን ዘግበዋል።