ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ አንድ መንገደኛ የዶሮ ስጋ ውስጥ ሽጉጥ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ሥር ዋለ
የአሜሪካ የትራንስፖርት ባለስልጣናት አንድ መንገደኛ በዶሮ ስጋ ውስጥ ሽጉጥ ደብቆ ለማለፍ ሲሞክር በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን አስታወቁ።
ፍሎሪዳ በሚገኘው ሎውደርዴል-ሆሊዉድ አየር ማረፊያ ውስጥ ነው የአሜሪካ የትራንስፖርት ደህንነት አስተዳደር ሰራተኞች የጦር መሳሪያውን በዶሮዋ ሆድ ውስጥ ያገኙት።
ተሳፋሪው አውሮፕላኑን ከመሳፈሩ ቀደም ብሎ በሚገኘው የፍተሻ ቦታ ነው በወረቀት በተጠቀለለው የዶሮ ስጋ ውስጥ የጦር መሳሪያውን ደብቆ የተገኘው።
የትራንስፖርት ደኅንነት ሰራተኞቹ ታዲያ ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን በማምጣት ተሳልቀውበታል። ጦር መሳሪያው ጥሬ የዶሮ ስጋ ውስጥ መገኘቱን ተከትሎ "እቅዱ ግማሸ መንገድ እንኳን አልበሰለም’’ ሲሉ ተሳልቀውበታል።
ባለስልጣናቱ እስካሁን ድረስ ይህንን ያደረገው ግለሰብ ማንነት ግልጽ ባያደርጉም የዶሮ ስጋውን ከተጠቀለለበት ሲፈቱ እና ከውስጡ ሽጉጡን ሲያወጡ የሚያሳየውን ምስል በኢንስታግራም ገጽ ላይ አጋርተዋል።
ዓመታዊው የምስጋና በዓል (ታንክስጊቪንግ) መቃረቡን ተከትሎ የትራንስፖርት ኤጀንሲው ሰራተኞች የተጓዞችን ደኅንነተ ለመጠበቅ ጠንክረው እንሚሰሩም ባለስልጣኑ ገልጿል።
‘’እንግዲህ እኛ እዚህ ጋር ዶሮውን እንጠብስላችኋለና። ነገር ግን ለበዓል የተገዛ ዶሮ ውስጥ የጦር መሳሪያ መደበቅ ግዜን ማባከን ነው። ይሄ ሃሳብም እንደዚሁ ግማሽ ያህል እንኳን አልበሰለም። ጥሬ ሃሳብ’’ ሲል የኢንስታግራም መልክቱ ያስነብባል።
ተወደደም ተጠላ የጦር መሳሪያ እና ጥይት ይዞ መጓዝን የተመለከቱ ሕግ እና ስርዓቶች አሉ ሲልም የትራንስፖርት ባለስልጣኑ አስታውሷል።
በአሜሪካ የጦር መሳሪያ ይዞ መጓዝ የሚፈቀድ ቢሆንም የራሱ መመሪያ አለው። ጥይቱ ከመሳሪው ውስጥ መውጣት እና በተቆለፈ ጠንካራ ሳጥን ውስጥ መግባት ይኖርበታል።
ባለስልጣኑ ባለፈው ዓመት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የጦር መሳርያ መያዙን እና ከዛ ውስጥም 85 በመቶው ጥይት የጎረሱ እንደነበሩም አስታውቆ ነበር።