አሜሪካ ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የምትፈልጋቸው የጤና መረጃዎች ምንድን ናቸው? ከሉዓላዊነት ጋርስ ምን ያገናኘዋል?

አሜሪካ በቅርቡ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር የገባችው የጤና ስምምነት ውዝግብ ፈጥሯል። ስምምነቱ በአንዳንድ አገራት ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን ሙሉ በሙሉ ያልተቀበሉትም አሉ።
ከእነዚህ መካከል ጋና፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ይገኙበታል።
ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው የተገለፀውን ይህንን የሁለትዮሽ ስምምነት በታኅሳስ 2018 ዓ.ም. ተፈራርማለች።
አሜሪካ ስምምነቱ የበሽታዎች መከላከል አቅምን እና የጤና ሥርዓትን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ ብትገልጽም፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች ስጋት አለኝ ብሏል።
ከኢትዮጵያ፣ ከኬንያ፣ ከሩዋንዳ፣ ከኡጋንዳ፣ ከናይጄሪያ እና ከሞዛምቢክ ጋር የተገቡ ስምምነቶችን ተመልክቻለሁ ያለው ተቋሙ ሰኔ ወር ላይ ባወጣው መግለጫ፣ አገራት በስምምነቱ አማካኝነት የጤና መረጃዎችን ለአሜሪካ እንደሚያቀርቡ ጠቅሷል።
ስምምነቱ የግለሰቦችን የጤና መረጃዎች አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችልም ገልጿል።
ለመሆኑ የጤና መረጃ ምንድን ነው? ለምንድን ነው የሚሰበሰበው? አሜሪካስ እነዚህን የጤና መረጃዎች ለምንድን ነው የምትፈልጋቸው?
በአሜሪካ ፔንሲልቫኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ኮሌጂ የኅብረሰተብ ጤና ሳይንስ ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶ/ር አበባየሁ ንጉሴ፣ የጤና መረጃ ከግለሰብም ሆነ ከኅብረተሰብ የሚሰበሰብ ማንኛውም ጤናን የተመለከተ መረጃ ነው ይላሉ።
እነዚህም የህመም ታሪኮች፣ የክትባት አገልግሎት መረጃዎች፣ የላብራቶሪ ምርመራ ውጤቶች እንዲሁም አንድ ሰው ሆስፒታል በሚሄድበት ጊዜ የሚሰጣቸውን ሌሎች መረጃዎችን ያካትታል።
የግለሰብ መረጃዎች፣ ዕድሜ፣ ፆታ፣ ገቢ፣ የቤተሰብ እና የአኗኗር ሁኔታ፣ የጋብቻ ሁኔታ እና በአጠቃላይ ማንነት የሚገልጹ መረጃዎች ናቸው።
የወረርሽኝ፣ የክትባት ታሪኮች፣ ጀኔቲክ (ዘረመል) መረጃዎች፣ የወሊድ እና የሞት ምጣኔ፣ ሥር የሰደዱ በሽታዎች እና ሌሎች መሰል መረጃዎች በማኅበረሰብ የጤና መረጃ ይካተታሉ።
እነዚህ የጤና መረጃዎች ከሆስፒታል እንዲሁም በጥናት መልክ ማኅበረሰቡ ውስጥ በመዝለቅ ቤት ለቤት በመጠይቆች አማካኝነት የሚሰበሰቡ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ እነዚህን መረጃዎች ከኅብረተሰብ ጤና ተቋማት እንዲሁም በአገር ውስጥ የተሰማሩ የውጭ ድርጅቶች ለሚሠሩት ሥራ ግብዓትነት ከማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚሰበስቧቸው መረጃዎች ማግኘት ይቻላል።
የስምምነቱ ዝርዝር ይፋ ስላልተደረገ "አሜሪካ ከኢትዮጵያ የምትፈልገው መረጃ የትኛው እንደሆነ ግልጽ አይደለም" የሚሉት ዶ/ር አበባየሁ፣ ስምምነቱ ከላይ ሲታይ የመረጃ ልውውጡ የአንድ ወገን እንደሚመስል ተናግረዋል።
"አሜሪካ ከተላላፊ በሽታዎች ጋር ተያይዞ ያሉ መረጃዎችን ከኢትዮጵያ እንደምትፈልግ" ገልጸዋል።
በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወቅት የነበረው የመረጃ ልውውጥ በፍጥነት ክትባት እንዲገኝ ማስቻሉን ያስታወሱት ዶ/ር አበባየሁ፣ እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን አስቀድሞ መሰብሰብ ጠቀሜታ አለው ይላሉ።
በመሆኑም በስምምነቱ የላብራቶሪ መረጃዎች፣ የወረርሽኝ ምልክቶች (ቅኝት) መረጃዎች እንዲሁም ዲጂታል መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ዕድል እንደሚኖር አመልክተዋል።
"በኢትዮጵያ በኩል ስምምነቱ የጤና ሥርዓትን ለማጠናከር ይውላል ቢባልም ሌሎች አገራት ስምምነቱ ላይ ጥያቄ ማንሳታቸውም የሚያመለክተው ነገር አለ" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, State House Kenya/fb
የጤና መረጃዎች ጥቅም እና ጉዳት ምንድን ነው?
'ቅድሚያ ለአሜሪካ' የተሰኘው እና የዓለም አቀፍ ጤና ስትራቴጂ አካል በሆነው የሁለትዮሽ ስምምነት መሠረት አሜሪካ በአምስት ዓመት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ትሰጣለች።
የፕሮጀክቱን አፈፃፀም መሠረት በማድረግ 150 ሚሊዮን ዶላር እንደምትጨምር ተገልጿል። ኢትዮጵያ ደግሞ 450 ሚሊዮን ዶላር የጤና ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ገብታለች።
የገንዘብ ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መግለጫ፣ ስምምነቱ የኢትዮጵያን የበሽታዎች መከላከል አቅም እና የጤና ሥርዓትን ለማጠናከር ያለመ እንደሆነ አስታውቋል።
የአሜሪካ ኤምባሲም ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከመደገፍ በተጨማሪ "አሜሪካውያን ዜጎችን ከዓለም አቀፍ የጤና ስጋቶች እንደሚጠብቅ ገልጿል።
ዶ/ር አበባየሁም አገራት የሚያደርጓቸው የጤና መረጃ ልውውጦች ወረርሽኞችን ለመከላከል፣ ለምርምር ሥራዎች እና ለቴክኖሎጂ ሽግግሮች ወሳኝ መሆናቸውን ይናገራሉ።
ያደጉ አገራት ወረርሽኞችን በተከሰቱበት ቦታ ለመቆጣጠርና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት እንዲህ ዓይነት መረጃዎችን ይፈልጋሉ።
"መረጃዎቹ ሥርጭቱን ለማየትና የበሽታ መነሻዎችን ለማወቅ ወሳኝ እንደሆኑም" በዲሞክራቲ ኮንጎ የተከሰተውን የኢቦላ ወረርሽኝ በማሳያነት ጠቅሰዋል።
በማደግ ላይ ያሉና ድሃ አገራትም በራሳቸው አቅም መረጃዎችን አስቀድሞ በመሰብሰብና ፈጣን ምላሽ በመስጠት በሽታዎችን መቆጣጠር እንዲችሉ ያላቸውን የጤና ሥርዓት ለማጠናከር ይረዳል።
"የእኛ አገር የጤና ሥርዓት ራሱን የቻለ አይደለም፤ በውጭ የሚደገፍ ነው። ከበጀትም አንፃር ሰፊ ክፍተቶች አሉ" የሚሉት ዶ/ር አበባየሁ፣ በጊዜ ሒደት አገሪቷ ጥገኛ እንዳትሆን ለማድረግም አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
ነገር ግን "መረጃዎቹ እንዴት ነው የሚሰበሰቡት፣ እንዴት ነው የሚጠበቁት? ለሦስተኛ ወገን ተላልፈው ላለመሰጠታቸው ምን ማረጋገጫ አለ? ይህስ በስምምነቱ ውስጥ ተካቷል ወይ?" የሚለው ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ይናገራሉ።
የግለሰብም ሆኑ የኅብረተሰብ የጤና መረጃዎች ሦስተኛ ወገን በሆኑት መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች ይፈለጋሉ።
በተለይ የዘረ መል መረጃዎች ለምርምርም ሆነ መድኃኒት ለማምረት ትልቅ ግብዓት ናቸው።
ስምምነቱ እነዚህን ጉዳዮች ከግምት ሳያስገባ የተካሄደ ከሆነና ለምን ዓላማ እንደሚውል መረጃው ሳይገለጽ፣ ያለ ፈቃድ ለሦስተኛ ወገን የሚተላለፍ ከሆነ "የሕግ ጥሰት" እንደሆነም አስረድተዋል።
የተለያዩ አገራት መረጃዎችን የሚጠብቁበት የየራሳቸው ሕጎች ያሏቸው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችም አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of Finance - Ethiopia
በኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 1321/2016፣ የሕግ ትርጓሜ የዘረመል ዳታ ማለት አንድ ግለሰብ በተፈጥሮ የወረሳቸው ወይም ያገኛቸው አጠቃላይ ባህሪያት የሚይዝ ሲሆን፣ በተለይ ከግለሰቡ በተወሰዱ የሥሪተ ሕይወት ናሙናዎች ትንተና መሠረት ስለአንድ ግለሰብ ፊዚዮሎጂ ወይም ጤና የተለየ መረጃ የሚሰጥ የግል መረጃ ነው።
ይህ መረጃ ጥንቃቄ ከሚፈልጉ መረጃዎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ያለባለቤቱ እውቅና እና ፈቃድ እንዲሁም መጠቀምን ሊፈቅዱ ከሚችሉ ሁኔታዎች ውጪ መጠቀምን ይከለክላል።
"እነዚህ መረጃዎች ለንግድ ማለትም በቴክኖሎጂው ዘርፍ መሣሪያዎችን (ቱልስ) ለመሥራት ሊውሉ ወይም ድርጅቶች ለተለያዩ ዓላማዎች ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ" የሚሉት ዶ/ር አበባየሁም፣ መረጃዎቹ በፈቃድ ሊሰበሰቡና ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሆኖም በቅርቡ ኢትዮጵያ የተፈራረመችው ስምምነት የግለሰቦችን እና የማኅበረሰብ የጤና መረጃዎችን አደጋ ላይ ሊጥል ይችላል የሚሉ ስጋቶች አሉ።
ተመሳሳይ ይዘት እንዳለው የተገለፀው ስምምነት የቀረበላት ዚምባብዌ ለአሜሪካ የፋርማሱቲካል ኩባንያዎች ይሰጣሉ የተባሉ የጤና መረጃዎች ምክንያት ስምምነቱን ውድቅ እንዳደረገች ገልጻለች።
የአገሪቱ መንግሥት ቃል አቀባይ፣ ከዚምባብዌ በሚወሰደው የበሽታ አምጪ ተዋህስያን መረጃ አማካኝነት የሚሠራ መድኃኒት ወይም ክትባት ለአገሪቱ ሕዝብ ይቀርብ እንደሆነ ማረጋገጫ አለመኖሩን ተናግረዋል።
ባዮሎጂካል መረጃዎች 'እንደ የጦር መሣሪያ'
የጤና መረጃዎች ጥበቃ የአንድ አገር ሉዓላዊነት ከሚከበርባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በተለይ ባዮሎጂካል (ሥነ ሕይወታዊ) መረጃዎች እንደ ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ።
ዶ/ር አበባየሁ ደኅንነታቸው ያልተጠበቁ የጤና መረጃዎች የአንድን አገር ሉዓላዊነት ስስ እና ተጋላጭ ያደርጉታል ይላሉ።
እነዚህ መረጃዎች አደባባይ ላይ የሚሰጡ ከሆነ ጠላት የሚባሉ አገራት ሊጠቀሙበት እንደሚችሉም ያስረዳሉ።
"የጤና መረጃ ባዮሎጂካል ዌፐን (መሣሪያ) ነው" የሚሉት ዶ/ር አበባየሁ፣ ኃያላን አገራት እንዲህ ዓይነት መረጃዎች የማይለዋወጡት ወይም ውስን የሆነ የመረጃ ልውውጥ የሚያደርጉት በዚህ ምክንያት እንደሆነ አብራርተዋል።
"በተለይ ባዮሎጂካል መረጃዎች በቤተ ሙከራ ውስጥ ነው የሚሠሩት፤ እንዲህ ዓይነት ክስተቶች በቀላሉ ማኅበረሰብን ለአደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ" ብለዋል።
ለዚህም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በጓቲማላ የተከሰተውን ታሪካዊ የጤና ክስተት ለአብነት ማንሳት ይቻላል።

በዚህ ጦርነት አሜሪካ የፓናማ ቦይን ለመጠበቅ ጦሯን እና አየር ኃይሏን በጓቲማላ አስፍራ ቆይታለች።
ያኔ የአሜሪካ ተመራማሪዎች ፔኒሲሊን የተባለውን ፀረ ባክቴሪያ መድኃኒት ለመሞከር ሆነ ብለው በሺዎች የሚቆጠሩ ጓቲማላውያንን በጨብጥ እና ቂጥኝ በሽታ እንዲያዙ አድርገው ነበር።
ይህን ያደረጉት መድኃኒቱን በተለያየ የዓለም ክፍል ላሉ ወታደሮቻቸው ለመስጠት በማለም ነው።
ድርጊቱ "በሰው ልጅ ላይ የተፈፀመ ወንጀል" ተብሏል። በዚህ ሙከራ የአዕምሮ ህመምተኞች፣ እስረኞችና በወሲብ ንግድ የተሰማሩ ሴቶች ያለፈቃዳቸው ሆነ ተብሎ በቫይረሱ እንዲያዙ ተደርገዋል። ሙከራው ሲደረግ በአሜሪካና በጓቲማላ ባለሥልጣናት መካከል ትብብር እንደነበር ተነግሯል።
የአሜሪካ መንግሥት ለተፈጠረው ክስተት ይቅርታ ጠይቋል።
ለዚህም ነው አገራት በግዛታቸው ውስጥ የሚሰበሰበው መረጃ ለምን እና በማን እንደሚሰበሰብ፣ ማን እንደሚጠቀምበት እንዲሁም መዳረሻው የት እንደሆነ ማወቅ ያለባቸው።
በግለሰብ ደረጃም ቢሆን ያለግለሰብ ፈቃድ የተሰጠ መረጃ ለመገለልና ለመድልዎ በማጋለጥ ሌላ በሽታ ሊያስከትል ይችላል። ለወረርሽኞች ስያሜ ሲሰጥ ጥንቃቄ የሚደረግበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው።
"ይህ ማለት ግን መረጃ መለዋወጥ አያስፈልግም ፤ የለብንም ማለት አይደለም" ያሉት ዶ/ር አበባየሁ፣ ነገር ግን የጤና መረጃዎች ደኅንነት ሊጠበቅ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።
ኃያላን አገራት የጤና መረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ?
አገራት የጤና መረጃን ጉዳይ በትኩረት ነው የሚመለከቱት። ሆኖም የጤና መረጃዎችን መለዋወጥ አዲስ ነገር አይደለም።
የምዕራብ እና የምሥራቅ ኃያላን አገራትም በጥብቅ የሕግ እና አፈፃፀም ማዕቀፎች የመረጃ ልውውጥ ያደርጋሉ። ይህም ስምምነት ላይ በሚደርሱ አገራት ብሔራዊ የደኅንነት እና ግላዊ መረጃ ጥበቃ ሕጎች ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
"በምዕራባውያኑ መካከል የመረጃ ልውውጥ ቢኖርም ውስንነቶች አሉ" ይላሉ ዶ/ር አበባየሁ።
አጋር ካልሆኑ አገራት ጋር ያለው ሲታይ ደግሞ ጉዳዩ ውስብስብ ሊሆን ይችላል።
እነዚህ አገራት እርስ በርስ በጠላትነት ስለሚተያዩ እና በሽታዎችን የመሥራት አቅም ስላላቸው በቁራኛ ሊተያዩ ይችላሉ።
አገራቱ በቀጥታ የመረጃ ልውውጥ ባያደርጉም፣ በርካታ አገራት አባል በሆኑበት የዓለም ጤና ድርጅት አማካኝት መረጃዎችን መለዋወጥ ሊኖር ይችላል።
በኮቪድ -19 ወረርሽኝ ወቅት የመረጃ ልውውጥ ዋነኛ የውዝግብ ማዕከል እንደነበር ይታወሳል።
የወረርሽኙ መነሻ እንደሆነች የተገለፀችው ቻይና መረጃዎችን ደብቃ መቆየቷ ወረርሽኙ እንዲዛመት አድርጋለች፤ በዚህም ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለሞት ዳርጋለች የሚል ክስ ይቀርብባታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ቫይረሱን 'ቻይና ቫይረስ' ብለው የጠሩት ሲሆን፣ ቻይና ስለበሽታው ለዓለም ሕዝብ ቀደም ብላ ማሳወቅ ነበረባት ሲሉ ተችተዋል።
በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸውም የዓለም ጤና ድርጅት ወረርሽኙን ለመግታት ያደረገው ጥረት አንስተኛ ነው፤ እንዲሁም ድርጅቱ በቻይና ቁጥጥር ሥር ወድቋል ሲሉ አገራቸውን ከድርጅቱ አባልነት አስወጥተዋል።
ኮቪድ ከቻይና ነው የተነሳው የሚለውም እስካሁን ድረስ አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
"በኢትዮጵያ ውስጥ 'አተት' የሚባል ነገር ባይኖርም ተመሳሳይ ምልክት ያለው ወረርሽኝ ሲያጋጥም ስሙን ይጠቀሙበታል" የሚሉት ዶ/ር አበባየሁ፣ ይህን የሚያደርጉት ይፋ መውጣቱ ቱሪዝም እና ሌሎች ነገሮችን ሊጎዳ ስለሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።
በመሆኑም አገራትን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ጥንቃቄ የተሞላበት የመረጃ ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
ወዳጅ ያልሆኑ ኃያላን አገራት በቀጥታ የመረጃ ልውውጥ የማያደርጉት በደኅንነት ስጋት ምክንያት እንደሆነም ይናገራሉ።
ወደየአገራቱ ለጥናት እና ምርምር የሚገቡ ተቋማት እና ተመራማሪዎች ላይም ክትትል እንደሚደረግ ይጠቅሳሉ።
በደቡብ እስያ እና በአፍሪካ ባሉ አገራት ግን ወትሮም እንደ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ባሉ ተቋማት መረጃዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን፣ አብዛኞቹ እነዚህ መረጃዎች ግን ግለሰባዊ እንዳልሆኑ ዶ/ር አበባየሁ አመልክተዋል።
"የሚሰበስቡት መረጃ ጥናት ከተካሄደበት በኋላ ለፖሊሲ ለውጥ እና ለዕቅድ የሚውል ነው" ብለዋል።
ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት ?
የኢትዮጵያ ጤና ባለሥልጣናት ስለመግባቢያ ስምምነቱን በዝርዝር ያሉት ነገር የለም።
ቢቢሲ ከጤና ባለሥልጣናት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ለሚኒስቴሩ የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳን እንዲሁም የጤና ሚኒስትሯን ዶ/ር መቅደስ ዳባን ለማነጋጋር ያደረጋቸው ሙከራዎችም አልተሳኩም።
ሆኖም ከኢትዮጵያ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት እንዲፈራረሙ የተጠየቁ አገራት ስምምነቱን ተቃውመውታል።
ውሉ አሜሪካ የአገራትን የጤና መረጃዎች እንድታገኝ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የታካሚዎች መረጃ እንዲሁም እንደ ቫይረስ፣ ባክቴሪያ እና ፓራሳይት ያሉ በሽታዎችን ከሚፈጥሩ ተህዋስያን ጋር የተያያዙ መረጃዎች በስምምነቱ ተካትተዋል።
ኢትዮጵያ የገባችው ስምምነት ዝርዝር ባይታወቅም "እንዲህ ዓይነት አገራዊ ስምምነቶች በፓርላማ የጤና ንዑስ ኮሚቴ በኩል ታይቶ ማለፍ" እንደነበረበት ዶ/ር አበባየሁ ተናግረዋል።
ሌሎች አገራት እንዳደረጉት የሚሰጠውን መረጃ እና የተገባውን ስምምነት በተመለከተ መመርመር እንደሚገባትም አክለዋል።
"የሚሰጠው መረጃ ምን ዓይነት ነው? ግለሰባዊ መረጃዎችን ያጠቃልላል ወይ? እንዴት ነው የሚጠበቁት? ሦስተኛ ወገን እነዚህን መረጃዎች ማግኘት ይችላል ወይ? የሚለው በጥልቀት ሊታይ ይገባል" ብለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ መረጃውን የሚሰጡ ሰዎች ሊያውቁ እና ሊፈቅዱ እንደሚገባ አስረድተዋል።
"በተለይ ከዘረ መል እና ባዮሎጂካል ጋር የተያያዙ መረጃዎች ከሆኑ የተፈለገው ከወረርሽኝ መከላከል ጋር ምን ያገናኘዋል?" የሚለው በደንብ መታየት እንደሚኖርበት መክረዋል።
የጤና ማኅበራትን፣ የሕግ ባለሙያዎችን ያካተተ ውይይት ተደርጎ መረጃው ለሕዝብ ግልጽ መደረግ አለበትም ብለዋል።















