በጋዛ ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ አንዲት ሕጻን በፖሊዮ ተያዘች

የፎቶው ባለመብት, REUTERS/Ramadan Abed
በጋዛ አንዲት የ10 ወር ጨቅላ ሕጻን በፖሊዮ ከተያዘች በኋላ ከፊል አካሏ እንደማይንቀሳቀስ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣናት ተናገሩ።
እንደ ተመድ ከሆነ ጦርነት ውስጥ ከገባች 11ኛ ወሯን በያዘችው ጋዛ ሰኔ ወር ላይ ከቆሻሻ ውሃ ከተሰበሰበ ናሙና ዓይነት ሁለት [ታይፕ 2] ፖሊዮቫይረስ ተገኝቶ የነበረ ቢሆንም ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በፖሊዮ የተያዘ አንድም ሰው አልተመዘገበባትም ነበር።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም አሁን ላይ በቫይረሱ የተያዘ ሰው መገኘቱ እጅጉን እንዳሳሰባቸው ገልጸው፣በሚቀጥሉት ሳምንታት ክትባት ለማሰራጨት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ክትባት ያልተከተበችው የ10 ወሯ ሕጻን በአንድ እግሯ ላይ ፓራሊስስ [ የነርቭ ጉዳት] የታየ ሲሆን አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንዳልሆነች ተገልጿል።
ፖሊዮቫይረስ ብዙውን ጊዜ የሚተላለፈው በቆሻሻ ፍሳሽ እና በተበከለ ውሃ አማካኝነት ሲሆን የመተላለፍ እድሉም ሰፊ ነው።
ቫይረሱ በተለይ በእግር አካባቢ ልምሻ [ያልተስተካከለ የሰውነት አቋም] የሚያስከትል ሲሆን በአብዛኛው ከ5 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ያጠቃል።
የሰብዓዊ እርዳታ ቡድኖች በጋዛ ከአስርት ዓመታት በኋላ እንደገና ለተከሰተው ፖሊዮ ምክንያቱ በጦርነቱ ምክንያት የሕጻናት ክትባት መቋረጡ እና በውሃ እና በፍሳሽ አወጋገድ ሥርዓቱ የደረሰው ውድመት ነው ብለዋል።
የበሽታውን ሥርጭት ለመግታትና ዕድሜያቸው ከ10 ዓመት በታች ለሆኑ ከ640 ሺህ በላይ ሕጻናት የፖሊዮ ክትባት ለማዳረስ ጦርነቱ ለሳምንት ያህል ጋብ እንዲልም ተመድ እየጠየቀ ነው።
የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “በጋዛ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት አደጋ ላይ ናቸው” ብለዋል።
በመሆኑም የክትባት ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን ክትባቱንና አስፈላጊ የሕክምና ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በቂ ነዳጅ፣ ጥሬ ገንዘብ መጨመር እና ትክክለኛ የሆነ ኮሚዩኒኬሽን እንደሚያስፈልግ እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች እና ወደ ጤና ተቋም የሚመጡ ሰዎች ደኅንነትም ሊረጋገጥ ይገባል ብለዋል ዋና ጸሐፊው።
የዓለም ጤና ድርጅት 1.6 ሚሊዮን ክትባቶችን እንዲሰራጩ የፈቀደ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን ድርጅት [ ዩኒሴፍ] አቅርቦቱን ለማዳረስ እያስተባበረ ነው። ዩኤንርዋ [UNRWA] የጤና ባለሙያዎች ቡድን ደግሞ ክትባቱ በጋዛ ከደረሰ በኋላ ይቆጣጠራሉ ተብሏል።
የዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር ካትሪን ሩስል ቫይረሱ ከ25 ዓመታት በኋላ በጋዛ መገኘቱ የተመሰቃቀለ፣ ተስፋ አስቆራጭ እና አደገኛ ሁኔታ መኖሩን ያሳያል ብለዋል።
ነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ የእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) ጦርነቱ ከጀመረ አንስቶ 2 ሚሊዮን 821 ሺህ 260 ሰዎችን ለመከተብ በቂ የሆነ ወደ 282 ሺህ 126 የፖሊዮ ክትባቶችን ወደ ጋዛ መላኩን ገልጾ ነበር።
መከላከያ ኃይሉ ጨምሮም በሚቀጥሉት ሳምንታት ከ1 ሚሊዮን በላይ ሕጻናትን ለመከተብ ተጨማሪ 60 ሺህ ክትባቶች እንደሚላክ ገልጿል።
እንደ አይዲኤፍ ከሆነ ለክትባት እና ወረርሽኞችን ለመከላከል ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባት የሚቻለው በግዛቷ ውስጥ ባለው የመንግሥት አስተባባሪዎች አማካይነት ነው።
እስራኤል በጋዛ ላይ የጦርነት ዘመቻ የጀመረችው መስከርም ወር መጨረሻ ላይ በደቡባዊ ግዛቷ በሐማስ ታጣቂዎች በተፈፀመባት ድንገተኛ ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች ከተገደሉ እና 251 ሰዎች ታግተው ከተወሰዱ በኋላ ነበር።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮም በጋዛ ከ40 ሺህ 265 በላይ ሰዎች መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
ሆኖም ሚኒስቴሩ ከሟቾቹ መካከል ሲቪል ሰዎች ምን ያህሎቹ እንደሆኑ አልጠቀስም። የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጽ/ቤት ከተገደሉት መካከል አብዛኞቹ ሕጻናት እና ሴቶች ናቸው ብሏል።












