ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያን ድንበር ጥሶ መግባት ‘ቀላል ነበር’ ሲሉ የዩክሬን ወታደሮች ተናገሩ
የዩክሬን ወታደሮች በመቶ ኪሎሜትሮች ርቀት ወደ ሩሲያ ግዛት ከገቡ በኋላ የሞስኮን ድንበር ጥሶ መግባት ቀላል ነው አሉ።
ሩሲያ ዩክሬንን ስትወር እንደ ምልክት ያስቀመጠችውን “Z” ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት ስትገባ እየተጠቀመበችበት ትገኛለች።
በወታደራዊ ተሽከርካሪ፣ በታንክና በሌሎችም መሣሪያዎች ላይ ዩክሬን ይሄንን ምልክት እያኖረች ነው።
ዩክሬን በመቶ ኪሎሜትሮች የሚቆጠር የሩሲያ ግዛትን ይዛለች። በጦርነቱ በዩክሬን ወገን የተመዘገበ ከፍተኛ ውጤት ነው።
በድንበር ያለው ኩርስክ ግዛት አስተዳዳሪ እንዳሉት ዩክሬን ከሩሲያ መኖሪያ አካባቢዎች 28ቱን የያዘች ሲሆን፣ ወደ 200,000 የሚጠጉ ሩሲያውያን ተፈናቅለዋል።
የዩክሬን ወታደሮቹ ቶማሽ እና አኮርድ በዚህ ውጤት ደስተኛ ናቸው።
ድንበር አልፎ መዝለቅ የተቻለው ሰው አልባ አውሮፕላናቸው ለሁለት ቀናት ባደረገው ትግል ነው።
“ወደዚህ እንድንመጣ ትዕዛዝ ሲሰጠን ምን ማለት እንደሆነ አላወቅንም ነበር። የጠላቶቻችንን የመገናኛና የስለላ መስመሮች ቆርጠናል” ይላል ቶማሽ።
በትክክል ምን ያህል የሩሲያ ግዛትን በቁጥጥር ሥር እንዳስገቡ ግልጽ አይደለም።
ዋና ኃላፊው ኦልክሳንደር ሲራስኪ 1000 ስኩዌር ኪሎሜትር በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ነው ቢሉም ጥያቄዎች አሉ።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር እንዳሉት ዩክሬን ወደ ሩሲያ ግዛት የበለጠ ዘልቃ ለመግባት ፍላጎት አላት። ከዚህ ቀደምም እንደዚህ ተብሎ እምብዛም ትክክል ሳይሆን ቀርቷል።
ሆኖም ግን ዩክሬን በወታደራዊ ዘመቻው ለመቀጠል ቁርጠኛ ትመስላለች።
በአጎራባች ሱሚ ግዛት እአአ በ2022 ከታየው ወዲህ የአሁኑ ከፍተኛ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነው።
ያ ወቅት አካባቢው ነጻ የወጣበት ሲሆን፣ አሁን የታየው እንቅስቃሴ ላለፉት 18 ወራት ከታየው የላቀ ነው።
ምን ያህል ስኬታማ ይሆናል የሚለውን ለማወቅ ግን ጊዜው ገና ነው።
ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እንዳሉት ሩሲያ ወደ ዩክሬን መሣሪያ የምትተኩስባቸውን ቦታዎች ዒላማ አድርገዋል።
“ፍትሕና ሰላም” ቅርብ ናቸው ሲሉም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ዩክሬን ጠንካራ ወታደሮቿን ወደ ድንበር አካባቢ ልካለች። አብዛኞቹ ፈርጣማ ናቸው። ፊታቸው ላይ ድካም ይነበባል።
አንድ በሩሲያ ግዛት የሚገኝ የዩክሬን ወታደር በቴሌግራም በላከው መልዕክት እንደገለጸው፣ ለወራት የታቀደ ኦፕሬሽን ነው።
“አስደንግጠናቸዋል። ምንም መከላከል ሳይገጥመን በቀላሉ ነው የገባነው። ነሐሴ 6 በተለያየ አቅጣጫ ድንበር አልፈን ገብተናል” ብሏል።
“ወዲያው ምዕራባዊ የከተማዋ ክፍል ሱዳዛ ደርሰናል” ሲልም አክሏል።
የአየር ጥቃትና ውጊያ ሲባባስ በሁለቱም አገራት ድንበር ላይ ያሉ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል።
የዩክሬን ወታደሩ “እኛ ንጹኃን ሩስያውያንን አንነካም። ግን ለኛ አሉታዊ አመለካከት ነው ያላቸው። ስለ ሩስያ ወታደሮች የተሳሳተ መረጃም ይሰጡናል” ብሏል።
የዩክሬን ወታደሮች በካርኪቭ፣ ፖክሮቪስክ እና ቶርታስክ አቅጣጫዎች ነው እንዲገቡ የተደረገው።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የሩስያ ግዛት ለመያዙ “ተመጣጣኝ ምላሽ” እንደሚሰጡ ተናግረዋል።
የዩክሬን ወታደሮቹ ሚሻ እና ቫሌራ በፑቲን ዛቻ የፈሩ አይመስልም።
“መጀመሪያ ጥቃቱን የጀመረችው ሩሲያ ናት። እኛ አይደለንም። አሁን ምላሽ ሰጥተናል። ምን ማድረግ እንምንችል አሳይተናል” ይላል ቫሌራ።
ምዕራባውያን ዩክሬን ድንበር አልፋ ጥቃት እንድትፈጽም ይሁንታውን የሰጡ ይመስላል።
እስከባለፈው ሳምንት ድረስ በቦታው የሩስያ ወታደሮች ነበሩ። የሩስያ ወታደሮች ከዩክሬን በቁጥር ስለሚበልጡ፣ አሁንም ዩክሬን በኦፕሬሽኑ ስኬት ካላገኘች ስጋት አንዣቧል።
“እንደ ሱድዛ ያሉ ከተሞችን ተቆጣጥረን መቆየት አለብን። በዚያ መንገድ ነው የሩሲያን ግዛት ይዘን መቀጠል የምንችለው” ሲል የዩክሬን ወታደር ተናግሯል።
ከዚህ በኋላ ሩሲያ በዩክሬን መሬት ከመዋጋት ይልቅ በራሷ መሬት ለመዋጋት ትገደዳለች ብላ ዩክሬን ታምናለች።
ይህ የዩክሬን አፀፋዊ ምላሽ በሰላም ድርድር የሚኖራትን ሚና ከፍ ያደርጋል ብለው የሚያምኑ ዩክሬናውያን አሉ። በተቃራኒው የሰላም ንግግርን ሊያከስምም ይችላል።