በአሜሪካ ፊላደልፊያ ስድስት ሰዎችን ያሳፈረ የሕክምና ጄት በህንጻ ላይ ተከስክሶ ጉዳት ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Pennsylvania Representative Jared Solomon
በአሜሪካ፣ ፔንሲልቫኒያ ግዛት፣ በፊላደልፊያ ከተማ ሰሜን ምሥራቅ ክፍል አንድ አነስተኛ የሕክምና ማጓጓዣ አገልግሎት የሚሰጥ ጄት በርካታ ህንጻዎች በሚገኙበት ሰፈር ውስጥ ተከስክሶ ጉዳት ደረሰ።
የሕክምና አውሮፕላኑ ድርጅት-ሬስኪዩ ኤር አምቡላንስ በሰጠው መግለጫ እንዳለው ጄቱ አርብ ምሽት አንድ ታማሚ ሕፃንና አስታማሚዋን እናቷን እንዲሁም አራት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ እየተጓዘ ነበር ።
በአውሮፕላኑ ላይ ተሳፍራ የነበረችው ሕፃን ሕይወቷን አደጋ ላይ የሚጥል የጤና እክል የነበረባት ሲሆን በአሜሪካ ሕክምና አድርጋ ወደ ሜክሲኮ ቲጁዋና እየተጓዘች እንደነበር የአየር አምቡላንስ ድርጅቱ ቃል አቀባይ ሻይ ጎልድ ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግረዋል።
ከእናት እና ልጅ በተጨማሪም አብራሪው ፣ረዳት አብራሪው ፣ ዶክተር እና የድንገተኛ ሕክምና ባለሙያ በአውሮፕላኑ ውስጥ ነበሩ።
ቃል አቀባይዋ ለኤንቢሲ እንደተናገሩት የሕፃኗ ሕክምና ወጪ በሌላ ድርጅት የተሸፈነ ነበር።
"ታዳጊዋ በሕይወት ለመትረፍ ብዙ ታግላለች፤በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ ቤቷ ስትሄድ ይህ ገጠማት" ብለዋል።
አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢም ቤቶች እና ተሽከርካሪዎች በእሳት የተያያዙ ሲሆን መሬት ላይ የነበሩ ሰዎችም ለጉዳት መዳረጋቸው ተገልጿል።
የግዛቷ አስተዳዳሪ ጆሽ ሻፒሮ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ " የሕይወት መጥፋት እንደሚኖር እናውቃለን፤ አደጋው አሳዛኝ ነው" ብለዋል።
የፊላደልፊያ ከንቲባ ቺርል ፓርከር በበኩላቸው የከተማዋ ባለስልጣናት በአደጋው የደረሰው የጉዳት መጠን ምን ያህል እንደሆነ አለማወቃቸውን ገልጸው፤በአደጋው የተጎዱ ወገኖች በፀሎት እንዲታሰቡ ጠይቀዋል።
" ስብርባሪ ካያችሁ 911 ላይ ደውሉ፤ምንም ነገር በእጃችሁ አትንኩ" ሲሉም የከተማዋን ነዋሪዎች አሳስበዋል።
ሊርጀት 55 የተባለው አውሮፕላን ምሽት 10፡30 ተነስቶ ከሰሜን ምሥራቅ ፊላደልፊያ አየር ማረፊያ ከ6.4 ኪሎሜትር ያነሰ ርቀት ከተጓዘ በኋላ መከስከሱን የፌዴራል አቪየሽን አስተዳደር ገልጿል።
አስተዳዳሩ በመግለጫው እንዳለው አውሮፕላኑ ሚሶሪ ወደሚገኘው ስፕሪንግፊልድ ብራንሶን ብሔራዊ አየር ማረፊያ እየተጓዘ ነበር።
የአቪዬሽን አስተዳደሩ እና የብሔራዊ ትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ አደጋውን እየመረመሩ ነው።
የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችም በአደጋው ሥፍራ በአፋጣኝ መድረሳቸው ተገልጿል።
አደጋው የተከሰተው በአሜሪካ አምስተኛ ትልቅ ከተማ በሆነችው ፊላደልፊያ ሰው በሚበዛበት የገበያ ማዕከል በሚገኙበት ሥፍራ ነው።
የዓይን እማኞች በአካባቢው በተጎዱ ሰዎች እና በእሳት በተያያዙ ቤቶች ሳቢያ ትርምስ ነበር የሚታየው ብለዋል።
የወጡ ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት አውሮፕላኑ ተምዘግዝጎ ሲወድቅ እና በእሳት ሲቀጣጠል አሳይተዋል። በዚህም ተሽከርካሪዎች መውደማቸውን እና የተቀጣጠሉ የአውሮፕላኑ ስብርባሪዎች ወደ መንገድ ተፈናጥረው መውጣታቸውን የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል።
አንድ የዓይን እማኝ በአካባቢው እያሽከረከሩ እንደነበር እና ያልተለመደ ድምጽ መስማታቸውን፤ ከዚያም ፍንዳታ መከተሉን የአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ ገልጸዋል።
"ከዚያም ሁሉም ሰው መጮህ ጀመረ" ብለዋል የዓይን እማኙ።
ሌላ የዓይን እማኝ በበኩላቸው ሰማዩ በእሳት ውጋገኑ ሲበራ እና አውሮፕላኑ ከህንፃው ጋር ተጋጭቶ ሲፈነዳ መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በፊላደልፊያ የሜክሲኮ ቆንስላ በኤክስ ገጹ በአደጋው የተጎዱ ሜክሲኳውያን ወደ እርዳታ የጥሪ ማዕከል እንዲደውሉ አስታውቋል።
አደጋውን ተከትሎ ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት መግለጫ አስተዳደራቸው ክስተቱን እየተከታተለው እንደሆነ ገልጸዋል።
" በፊላደልፊያ አውሮፕላን መከስከሱ የሚያሳዝን ነው፤ተጨማሪ አሳዛኝ ነፍሶች ጠፍተዋል" ብለዋል።
ይህ አደጋ የተሰማው በዋሽንግተን ዲሲ አንድ የመንገደኞች አውሮፕላን እና የጦር ጀት ተጋጭተው የሁሉም 67 ተሳፋሪዎች ሕይወት ማለፉን ባለሥልጣናት ከገለጹ ከሁለት ቀናት በኋላ ነው።
ይህም ባለፉት 20 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ በርካታ ሰዎች ያለቁበት አስከፊው አደጋ ነው።












