የመንግሥታቱ ድርጅት የአልጀዚራ ጋዜጠኛ የተገደለችው በእስራኤል ጦር ነው አለ

ጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ሺሪን አቡ አቅላ
ታትሟል

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ታዋቂዋ የአልጀዚራ ጋዜጠኛ የተገደለችው በፍልስጤም ታጣቂዎች ሳይሆን ከእስራኤል ጦር ኃይል በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ ከድምዳሜ ደርሻለሁ ብሏል።

የጽህፈት ቤቱ ቃል አቀባይ የመንግሥታቱ ድርጅት ከዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሰው ከሳምንታት በፊት የተገደለችው ጋዜጠኛ ላይ "ገለልተኛ ክትትል" ካደረገ በኋላ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰው የጋዜጠኛ ሺሪን አቡ አቅላ ግድያ የተፈጸመው በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው ዌስት ባንክ ውስጥ ለዘገባ በተሰማራችበት ወቅት ነበር።

ለግድያው ፍልስጤም እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገች ሲሆን እስራኤል በበኩሏ መካሰስ እውነቱን አያወጣውም የሚል ምላሽ ስትሰጥ ቆይታለች።

የ51 ዓመቷ የፍልስጤም እና አሜሪካ ጥምር ዜግነት ያላት ጋዜጠኛ በቀጠናው ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ ልምድ እና ከበሬታን ያተረፈች ነበረች።

የእስራኤል ኃይል እና የፍልስጤም ታጣቂዎች ሲፋለሙበት ከነበረ አካባቢ አቅራቢያ በሚገኝ መንገድ ላይ ተተኩሶባት የተገደለችው ጋዜጠኛዋ “ፕሬስ” የሚል በጉልህ የሚታይ ጽሁፍ ያለው የጥይት መከላከያ ሰደርያ እና ቆብ አድርጋ ነበር።

ጋዜጠኛዋ የተገደለችው ከእስራኤል ጦር በተተኮሰ ጥይት እንደሆነ የዓይን እማኞች በወቅቱ ቢገልጹም፣ እስራኤል ግን አልቀበለውም ብላ ነበር።

የተተኮሰው ጥይት መነሻ እንዲጣራ ወይም የጋራ ምርመመራ እንዲካሄድ እስራኤል ስትጠየቅ አሻፈረኝ በማለቷ ጋዜጠኛዋን ማን እንደገደላት ማወቅ ከባድ ነው በማለት ፍልስጤማውኣን ገልጸው ነበር።

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤት ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳሳኒ ትላንት በጀኔቭ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ለጋዜጠኛዋ ሞት እና ለባልደረባዋ መጎዳት ምክንያት የሆነው ጥይት የተተኮሰው ከእስራኤል የፀጥታ ኃይሎች እንጂ ቀደም ብለው የእራኤል ባለሥልጣናት ሲናገሩ እንደነበረው ፍልስጤሞች ኢላማቸውን ሳይመርጡ በተኮሱት ጠይት አይደለም” ብለዋል።

“በጣም የሚያሳዝነው ነገር ደግሞ የእስራኤል ባለሥልጣናት ወንጀሉን ለማጣራት ምርመራ አለማድረጋቸው ነው” ሲሉም አክለዋል።

ቃል አቀባይዋ የተለያዩ መረጃዎች ከእስራኤል ጦር እና ከፍልስጤም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሲመጣ እንደነበር ጠቅሰው፣ ክስተቱ በተፈጸመበት ወቅት አራት ጋዜጠኞች ወደ መንገድ መውጣታቸው እና “በርካታ በተናጠል የተተኮሱ እንዲሁም ኢላማ መርጠው የተተኮሱ የሚመስሉ ጥይቶች የእስራኤል ጦር ከነበረበት አቅጣጫ ሲመጣ ነበር” ብለዋል።

“በተናጠል የተተኮሰ ጥይት አሊ ሳሙዲን ትከሻው ላይ መቶ ሲጎዳው፣ ሌላ ደግሞ የአቡ አቅላ ጭንቅላትን መትቶ ወዲያው እንድትሞት አድርጓል” ሲሉም አስረድተዋል።

የሰብአዊ መብቶች ጽህፈት ቤቱ ላወጣው መግለጫ ምላሽ የሰጠው የእስራኤል መከላከያ ኃይል ጥይቱ ከየት አቅጣጫ እንደተተኮሰባት ማረጋገጥ አይችልም ብሏል።

“የእስራኤል ጦር ኃይል ምርመራ የሚያሳየው ጋዜጠኛዋ ሆን ተብሎ እንዳልተተኮሰባት እና የፍልስጤም ታጣቂ ያለኢላማ ተኩሶ ይግደላት ወይም የእስራኤል ጦር ባለማወቅ ይገደላት ማወቅ አይቻልም” ብሏል።

እስራኤል ከየትኛው ወታደር በተተኮሰ ጥይት እንደተገደለች ለማወቅ ከረዳ በሚል የተገደለችበትን ጥይት የጠየቀች ቢሆንም ፍልስጤም እስራኤልን ስለማላምን አልሰጥም ብላለች።