ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ሚስቱንና ልጁን የገደለው የቀድሞ ጠበቃ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት
በአሜሪካ በርካቶችን ባስደነገጠ ሁኔታ ሚስቱንና ልጁን የገደለው የቀድሞ ጠበቃ አሌክስ መርዳው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
የደቡብ ካሮላይና ግዛት ፍርድ የተሰማው፣ ዳኞች በ54 ዓመቱ ግለሰብ ላይ ብይን ለመስጠት ለሦስት ሰዓታት ገደማ ክርክር ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ ነው።
የመርዳው ባለቤት የ52 ዓመቷ ማጌ እና የ22 ዓመት ወንድ ልጁ ፖል የተገደሉት እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 7፣ 2021 በቤተሰባቸው ግቢ ውስጥ ነበር።
አቃቤ ሕግ፣ የቀድሞ ጠበቃው ሚስቱንና ልጁን የገደለው ያለበትን የገንዘብ ወንጀል ትኩረት ለመቀየር እና ርህራሔ ለማግኘት ነው ሲል ተከራክሯል።
ዳኛ ክሊፍቶን ኒውማን ክሱን “ አስቸጋሪ ከሆኑት ውስጥ አንዱ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን “እውቅ የሕግ ማኅበረሰቡ አባል” የነበረውን የመርዳውን የኋላ ታሪክ መርምረዋል።
በችሎቱ ላይ “ሕግን መለማመድ የጀመርከው ከእኔ ቀድመህ ነበር።ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተገናኝተናል” ሲሉ የተናገሩት ዳኛው፣ መርዳው ግድያውን ከፈፀመ ከአንድ ዓመት በኋላ መከሰሱና መታሰሩን ማወቃቸው “ልብ ሰባሪ ነው” ብለዋል።
አሌክስ መርዳው ለበርካታ አስርት ዓመታት ከፍተኛ ቦታ የያዘውን ሕጋዊ ሥርዓት ይመራ ነበር።
የቀድሞው ጠበቃ በሁለቱ ሰዎች ግድያ ክስ የተመሰረተበት ከ6 ሳምንታት የፍርድ ሒደት በኋላ ነበር።
በፍርድ ሒደቱ መርማሪዎች፣ መርዳው ለሱስ እና የተንደላቀቀ ሕይወትን ለመምራት ከደንበኞቹ 9 ሚሊየን ዶላር መስረቁን ተናግረዋል።
አርብ ዕለት በተላለፈው ብይን ችሎት ወቅት መርዳው፣ ሁለት ጊዜ የተናገረ ሲሆን ጥፋተኛ አለመሆኑን ገልጿል።
ጠበቃውም የተላለፈበት የዕድሜ ልክ እስራት ላይ በአስር ቀናት ውስጥ ይግባኝ እንደሚጠይቁ ተናግረዋል።
በፍርድ ሒደቱ ላይ ከግድያው የተረፈው ልጁም ተገኝቶ በዝምታ ሲከታተል እንደነበር ተገልጿል።
ዳኛው ምን አልባት ግድያዎቹ የተፈፀሙት በአደንዛዥ እፅ ተፅዕኖ ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዋና አቃቤ ሕግ ክሬይተን ዎተርስ በበኩላቸው በደቡብ ካሮላይናው ጠበቃ ላይ የቀረቡት ማስረጃዎች “ በጣም በርካታ እንደነበሩ ገልጸው፣ “በራሱ ቤተሰብ ላይ ጭምር ራሱን ከሌሎች ሁሉ በላይ ያደረገ ተንኮለኛ ሰው መሆኑን አሳይተዋል”ብለዋል።
መርዳው ግን ጥፋተኛ አለመሆኑን ተከራክሯል። “ ሚስቴንና ልጄን በፍጹም አልጎዳም” ሲልም ለችሎቱ አስረድቷል።
የመርዳው ጠበቆች ቅጣቱ ከተላለፈ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ፣ መርዳው በችሎቱ ወቅት አቋም ይዞ መከራከሩ ስህተት ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል። ከመርዳው የገንዘብ ወንጀል ጋር የተያያዙ ማስረጃዎች በግድያው ችሎት ውስጥ እንዲካተቱ የፈቀደውን የዳኛ ኒውማን ውሳኔን ግን ስህተት ነው ብለዋል።
የእውቁ ጠበቃ ክስ አገራዊ ትኩረትን የሳበ ሲሆን እውነተኛ የወንጀል ድርጊቶች ላይ ያተኮሩ ፖድካስቶች እና ዘጋቢ ፊልሞች እንዲሰሩ ምክንያት ሆኗል።