ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢራን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለተቃውሞ አደባባይ መውጣቱን ቀጥሏል
በኢራን የተቃውሞ ሠልፍ ከጀመረ ከስድስት ሳምንት ወዲህ ትልቁ ነው የተባለ ተቃውሞ በበርካታ ከተሞች ተደረገ።
በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢራን ትልልቅ ከተሞች እንዲሁም ሌሎች ስፈራዎች ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸው ተገለጿል።
በኢራን ከስድስት ሳምንት በፊት የተቃውሞ ሠልፉ ከጀመረ ወዲህ የአሁኑ ግዙፉ ነው ተብሏል።
የተቃውሞ ሠልፉ የበረታው ማሻ አሚኒ የተባለች ኢራናዊት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ከሞተች 40 ቀን መሙላቱን ተከትሎ ነው።
ይህ የተቃውሞ ሠልፍ ለኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል።
በኖርዌይ መቀመጫውን ያደረገው የኢራን ሠብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድን፣ ቢያንስ 234 ተቃዋሚ ሠልፈኞች 29 ሕጻናትን ጨምሮ በፀጥታ አካላት ተገድለዋል ብሏል።
የኢራን ባለስልጣናት የተቃውሞ ሠልፉን በውጪ ኃይሎች “የተቀነባበረ” ሲሉ አጣጥለውታል።
በማህበራዊ ሚዲያ በሰፊው የተሰራጨ እና ቢቢሲ ትክክለኛነቱን ያረጋገጠው ተንቀሳቃሽ ምስል ረቡዕ ምሽት ግዙፍ የተቃውሞ ሠልፍ መካሄዱን ያሳያል።
በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን እንዲሁም ሌሎች ከተሞች በርካቶች በዋና አውራ ጎዳናዎች “ሞት ለአምባገነኖች” የሚል መፈክር እያሰሙ ሲጓዙ ተስተውለዋል።
ይህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተቃውሞ ሠልፍ የታየው ፖሊስ በማሻ አሚኒ የትውልድ ስፍራ፣ ሳቄዝ በተባለች ከተማ ተቃዋሚዎች ላይ ተኩስ መክፈቱን ተከትሎ ነው።
ማሻ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውላ የነበረው ሂጃቧን “በአግባቡ አልለበሰችም” በሚል ሲሆን በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለችም ሕይወቷ አልፏል።
የማሻ አሚኒ ሕይወቷ ካለፈ አርባ ቀን መሙላቱን ተከትሎ በርካቶች በተለያዩ ከተሞች በመሰባሰብ እና የተቃውሞ ድምጻቸውን በማሰማት አስበዋታል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በከተሞች ለተቃውሞ የወጡ ሠልፈኞች ላይ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ እና ጥይት መተኮሱን ገልፀዋል።
በዚህ የተነሳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም።
የ22 ዓመቷ አሚኒ ከሞተች ወዲህ የኢራን አደባባዮች እና ጎዳናዎች በተቃውሞ ሠልፈኞች መጥለቅለቃቸውን ቀጥለዋል።
አሚኒ በቴህራን በግብረገብ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ከዋለች ሶስት ቀን በኋላ ራሷን መሳቷን እና መሞቷ ይታወሳል።
በወቅቱ የፀጥታ አካላት ጭንቅላቷን ከመኪና ጋር እንዳጋጩት እና በዱላ እንደመቷት ሪፖርቶች ቢያሳዩም ፖሊስ ግን አስተባብሎ በልብ ድካም መሞቷን ገልጿል።
ቢቢሲ እና ሌሎች መቀመጫቸውን ኢራን ያደረጉ ገለልተኛ መገናኛ ብዙኀን በአገሪቱ ውስጥ እንዳይዘግቡ በመከልከላቸው በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን የሚወጡ መረጃዎችን ለማጣራት አዳጋች አድርጎታል።
የኢራን ባለስልጣናትም ኢንተርኔትን በተደጋጋሚ የሚያቋርጡ ሲሆን ተቃዋሚ ሠልፈኞች በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን ላይ መረጃ ለማጋራት አስቸጋሪ አድርጎባቸዋል።