አሜሪካ እጅግ ዘመናዊ የተባለ አዲስ የኑክሌር ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ሰራች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ አየር ኃይል ቢ-21 የተባለ አዲስ ከራዳር ዕይታ ውጪ የሚበር ኑክሌር ቦምብ ተሸካሚ የጦር አውሮፕላን ገንብቶ ይፋ አደረገ።
ይህ አዲስ ዘመናዊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላን በቀዝቃዘው ጦርነት ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ለበረራ የበቁትን ተመሳሳይ የጦር አውሮፕላኖች ቀስ በቀስ እንደሚተካ ተነግሯል።
ከ30 ዓመታት ወዲህ የተገነባው ይህ አዲሱ አውሮፕላን ለእያንዳንዱ ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪን የጠየቀ ሲሆን፣ ከኑክሌር በተጨማሪ ሌሎች መደበኛ የጦር መሳሪያዎችን መሸከም ይችላል።
እንደሚጠበቀውም አውሮፕላኑን የተመለከቱ ዝርዝር መረጃዎች በምስጢር በመያዛቸው ይፋ በተደረገበት ጊዜ የተባለ ነገር የለም።
የአሜሪካው የመከላከያ ኃላፊ ሎይድ ኦስቲን አውሮፕላኑን በተመለከተ “አሜሪካ ያላትን ዘላቂ አዳዲስ ፈጠራዎችን የማውጣት የበላይነት ማሳያ ነው” ብለዋል።
ቢ-21 የተባለው ይህ አዲስ የጦር አውሮፕላን ትናንት አርብ ካሊፎርኒያ ውስጥ በሚገኘው ኖርዝሮፕ ግሩማን በተባላው አምራቹ አማካኝነት በተካሄደ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው ይፋ የተደረገው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አውሮፕላኑ አሜሪካ ካሏት የጦር አውሮፕላኖች መካከል በከፍተኛ ደረጃ የረቀቀ መሆኑን የመከላከያ ባለሥልጣኑ ጠቅሰው “እጅግ ዘመናዊ የአየር መከላከያ ሥርዓቶች ሳይቀሩ ቢ-21 አውሮፕላንን በሰማይ ለመለየት ይቸገራሉ” ብለዋል ኦስቲን።
አውሮፕላኑ ሲገናባ አስፈላጊ ነገሮችን ለማካተት በሚያስችል ሥርዓት የተሰራ በመሆኑ “ወደፊት ሊፈጠሩ የሚችሉ የጦር መሳሪያዎችን ሳይቀር ለመያዝ ይችላል” ሲሉ አክለዋል።
በምርቃው ወቅት አውሮፕላኑን ያለሰው ስለማብረር የሚኖር ዕድልን በተመለከተ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ የአሜሪካ አየር ኃይል ቃል አቀባይ እንዳለችው ግን “ቢ-21ን ያለአብራሪ ስለማንቀሳቀስ የተሰጠ ውሳኔ ባይኖርም፣ አውሮፕላኑ ይህንን ለማድረግ የሚስችል አቅም አለው።”
ቢ-21 የመጀመሪያ በረራውን በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
አውሮፕላኑ አሜሪካ ያሏትን ቢ-1 እና ቢ-2 የተባሉትን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች ሞዴልን ቀስ በቀስ ይተካል ተብሏል።
ለዚህም 203 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ወጪን የሚጠቅይ ሲሆን፣ ግዢው እና ወደ ሥራ የማስገባቱ ሂደት ከ30 ዓመት በላይ ሊወስድ እንደሚችል ብሉምበርግ ዘግቧል።
የአውሮፕላኑ አምራች እንዳለው በአሁኑ ወቅት “አዲስ የአመራረት ዘዴን እና ግብአቶችን” በመጠቀም እጅግ ዘመናዊ የሆኑትን እነዚህን ስድስት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በመገንባት ላይ ነው።
የአሜሪካ አየር ኃይል ቢያንስ 100 የሚሆኑ ቢ-21 የተባሉት አዳዲስ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች እንዲኖሩት አቅዷል።












