ምዕራባውያን የሩሲያን ገቢ ለማዳከም በነዳጅ ምርቷ ላይ የዋጋ ገደብ ጣሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በሩሲያ ነዳጅ ላይ የተጣለው አዲሱ የዋጋ ጣሪያ “የፑቲን እጅግ ወሳኝ የገቢ ምንጭን በፍጥነት እንዲቋረጥ ያደርጋል” ስትል አሜሪካ ገለጸች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት የለን በአሜሪካ እና በአጋሮቿ ትላንት አርብ በይፋ የጸደቀው የዋጋ ገደብ ወራትን ከፈጀ ጠንካራ ሥራ በኋላ የተገኘ ነው ብለዋል።
ይህ የዋጋ ጣሪያ ባሕር በኩል ከሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ የሚያስገቡ አገራት በበርሜል ከ60 ዶላር በላይ እንዳይከፍሉ የሚያደርግ ነው።
ይህ ውሳኔ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ወይም ከዚያ ሳይርቅ ወደ ተግባራዊ ይሆናል።
ከዋጋ ጣሪያው ውሳኔ በነዳጅ እና ምግብ ዋጋ መናር ከፍተኛ ተጽእኖ የደረሰባቸው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የግምጃ ቤት ኃላፊዋ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የገንዘብ ምንጭ ላይ ጫና በማሳደር “በጭካኔ የተሞላውን ወረራቸውን ለመደጎም ጥቅም ላይ የሚያውሉትን ትርፍ ይገድባል” ብለዋል።
“ቀድሞውንም እየተጎዳ ያለው የሩሲያ ምጣኔ ሃብት እና በመስፋት ላይ ያለው የአገሪቱ በጅት ላይ በነዳጅ ዋጋ ላይ የተቀመጠው ጣሪያ የፑቲን ወሳኝ የትርፍ ምንጭን በፍጥነት እንዲገታ ያደርጋል” ብለዋል በጽሁፍ በሰጡት መግለጫ።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታደርገውን ጦርነት እንድትገታ የገንዘብ አቅሟን ለማዳከም በቅርቡ በተካሄደው የቡድን 7 አገራት [አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን እና የአውሮፓ ኅብረት] የዋጋ ጣሪያው ሃሳብ ለውይይት ቀርቦ ነበር።
ሁሉም የአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት እንዲቀበሉት የሚጠበቀውን የዋጋ ጣሪያ ፖላንድ እንድታምንበት ከተደረገ በኋላ ኅብረቱ አጽድቆታል።
ፖላንድ ውሳኔው የናዳጅ ዋጋን በ5 በመቶ ዝቅ እንደሚያደርገው ካረጋገጠች በኋላ ነው ለዋጋ ጣሪያው ድጋፏን የገለጸችው።
የአውሮፓ ኅብረት የነዳጅ ዋጋ ጣሪያው ከ65 እስከ 70 የአሜሪካን ዶላር እንዲሆን ሃሳብ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም፣ ፖላንድ እና ሉቲዋኒያ ዋጋው እጅግ ከፍ ብሏል በሚል ውሳኔውን ውድቅ አድርገውት እንደነበር ተሰምቷል።
ፖላንድ በተቻለ መጠን ዝቅ እንዲል ስትፈለግ የነበረ ሲሆን፣ እየተቀየረ ባለው የነዳጅ ዋጋ ጣሪያው ከገበያው ዋጋ በታች ሊሆን የሚችልበትን አማራጭ ስታጤን ነበር።
የቡድን 7 አገራት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አውስትራሊያ በጋራ ባወጡት መግለጫ የነዳጅ ዋጋ ጣሪያ የማስቀመጡን ውሳኔ አስፈላጊነት ሲገልጹ “ሩሲያ ዩክሬን ላይ ከፈጸመችው ወረራ የምታገኘውን ትርፍ ለመግታት” ያስችላል ብለዋል።
የብሪታኒያ ጀርሚ ሃንት አገራቸው ድጋፏን ከማድረግ እንደማትቆጠብ እና የፑቲንን የገንዘብ ምንጭ ለማመንመን ሌሎች አማራጮችን ከመፈለግ እንደማትቦዝን ገልጸዋል።
ይህ የዋጋ ጣሪያ ስምምነት ወደ ተግባር የሚቀየረው የአውሮፓ ኅብረት ወደ አባል አራት በሚገቡ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ላይ የጣለው እገዳ በሚተገበርበት ተመሳሳይ ቀን ነው።
አዲሱ የዋጋ ጣሪያ ውሳኔ በዓለም ዙሪያ ያለውን የነዳጅ ውጪ ንግድ ላይ ተጽእኖ የሚያስድር ነው።
በቡድን 7 አማካኝነት የቀረበውን የነዳጅ ዋጋ ጣሪያ ውሳኔን የፈረሙ አገራት በባሕር በኩል የሚያስገቡትን ነዳጅ መግዛት የሚችሉት በስምምነቱ በተቀመጠው ወይም ከዚያ በታች በሆነ ዋጋ ነው።
የዩክሬን ምዕራባውያን አጋሮች በዋጋ ጣሪያው ስምምነት ላይ ያልፈረሙ አገራት የሩሲያን ነዳጅ ለሚያደርሱላቸው ተሽከርካሪዎች የሚሰጠውን መድህን እንደሚከለክሉ ገልጸዋል። ይህም ሩሲያ ነዳጇን ከተቀመጠው ዋጋ በላይ እንዳትሸጥ የሚያደርግ ነው።
ውሳኔውን ያወገዘችው ሩሲያ የዋጋ ጣሪያ ስምምነቱን ለፈረሙ አገራት ነዳጅ አላቀርብም ብላለች።
በሩሲያ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴን የሚመሩት እና በአገሪቱ ከፍተኛ ፖለቲከኛ የሆኑት ሊዎንድ ስሉትስኪ፣ ባስቀመጠው የዋጋ ጣሪያ ሳቢያ የአውሮፓ ኅብረት የራሱን የነዳጅ ደኅንነት አደጋ ላይ እያጣለ ነው ብለዋል።
እንደ ዓለም አቀፉ የኢነርጂ ማኅበር መረጃ ከጦርነቱ በፊት ግማሽ የሚሆነው የሩሲያ ነዳጅ የውጭ ንግድ መዳረሻው አውሮፓ ሲሆን፣ ጀርመን ቀዳሚዋ የሩሲያ ነዳጅ ተጠቃሚ ናት። ኔዘርላንድ እና ፖላንድ ደግሞ ሁለተኛና ሦስተኛ ናቸው።
ሆኖም ከጦርነቱ በኋላ የአውሮፓ ኅብረት አገራት በሩሲያ ነዳጅላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው።
አሜሪካ የሩሲያን ድፍድፍ ነዳጅ ስታግድ ዩናይትድ ኪንግደም ደግሞ በተያዘው የፈንጆቹ ዓመት ማብቂያ ላይ ለማገድ አቅዳለች።
የሩሲያ ነዳጅ ላይ የሚደረገው የምዕራባውያኑ ጫና ሞስኮ ላይ ተጽእኖ ቢኖረውም፣ አሁን ላይ የሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ ቀዳሚ ገዢዎች በሆኑት እንደ ሕንድ እና ቻይና ባሉ ገበያዎች እየተካካሰ ነው።








