የቀድሞው የቻይና መሪ ጂያንግ ዜሚን በ96 ዓመታቸው አረፉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቻይና ካስመዘገበችው እድገት ጋር ከሚጠቀሱ መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት ጂያንግ ዜሚን በ96 ዓመታቸው ዛሬ ረቡዕ ማረፋቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።
ቻይና ፈጣን እና ከፍተኛ መጠን ያለው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ባስመዘገበችበት እና ለቀሪው ዓለም እራሷን ክፍት ባደረገችበት ወቅት መሪ የነበሩት ጂያንግ ዜሚን በአገሪቱ የእድገት ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ መሪ ናቸው።
አስካሁን ቻይናን የሚያስወቅሳት የታይናሚን አደባባይ የተማሪዎች ተቃውሞን የቻይና መንግሥት በኃይል ከተቆጣጠረ በኋላ ነበር ዜሚን ወደ አገሪቱ መሪነት የመጡት።
በቅርቡ የቻይና ታሪክ ውስጥ ቀዳሚ ከሆኑት መሪዎች አንዱ የሆኑት ዜሚን ለአገሪቱ እድገት ወሳኝ በሆኑ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ላይ የጎላ አሻራ እንዳለቸው ይነገራል።
ዜሚን በመሪነት ዘመናቸው ዩናይትድ ኪንግደም ሆንግ ኮንግን ለቻይና በሰላም እንድታስረክብ ያደረጉ ሲሆን፣ ቻይና ወደ ዓለም የንግድ ድርጅት እንድርገባ በማድረግ ምጣኔ ሀብቷ ከቀሪው ዓለም ጋር እንድትተሳሰር አድርገዋታል።
በሥልጣን ዘመናቸው ቻይና ጠንካራ ኢኮኖሚ ስትገነባ፣ ኮሚኒስቶች ደግሞ የአገሪቱ ሥልጣን ላይ ያላቸውን ቁጥጥር የበለጠ አጠበቁ እንዲሁም አገሪቱ ከዋናዎቹ የዓለም ኃያላን ተርታ ተሰለፈች።
ከስኬታቸው በተጨማሪም ለአገሪቱ ኮሚኒስት ፓርቲ ስጋት ነው በሚል በቻይና ውስጥ ሕገ ወጥ በተደረገው የፋሉን ጎንግ የእምነት ቡድን ላይ በወሰዷቸው ከባድ የቁጥጥር እርምጃዎች ትችት ይቀርብባቸው ነበር።
ጂያንግ ዜሚን በአውሮፓውያኑ 1989 በርካቶች የተገደሉበት የታይናሚን አደባባይ ተቃውሞ ከተካሄደ እና በዚህም ሳቢያ ቻይና በዓለም አቀፍ ደረጃ ውግዘት እንዲሁም መገለል ከደረሰባት በኋላ ነበር ሥልጣን የያዙት።
በቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ውስጥ ባሉ የለውጥ አቀንቃኞች እና ለውጡን በሚቃወሙ ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተካሄደው የሥልጣን ፉክክር በኋላ ነበር ዜሚን ወደ መሪነት የመጡት።
ይህም በፓርቲው ውስጥ ጉልህ ሚና ያልነበራቸውን እና ብዙም ትኩረት ያላገኙትን ጂያንግን ለከፍተኛው ሥልጣን እንዲበቁ በሩን ከፍቶላቸዋል።
የእሳቸው ሹመት በፓርቲው ከፍተኛ አመራር ውስጥ ባሉት ሁለት ኃይሎች መካከል የነበረውን ፍጭት ለማስታረቅ በሚል የተፈጠረ ዘዴ ነበር።












