ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጣሊያን የተገደለው ናይጄሪያዊ ባለቤት ፍትህ እንዲሰጣት ጠየቀች
በጣሊያን በጎዳና ንግድ ላይ የተሰማራው ናይጄሪያዊ “አሳዛኝ አሟሟትን” ተከትሎ ፍትህ ይሰጠኝ ስትል ሚስቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቆይታ ጠየቀች።
የ39 ዓመቱ አሊኩ ኦጎርቹክዉ በባሕር ዳርቻዋ ሲቪታኖቫ ማርቼ ከተማ ነበር የሚነግደው። አርብ ዕለትም መሐረቦቹን እየሸጠ ሳለ ነበር በአንድ ግለሰብ ተሳዶ መገደሉ ተዘግቧል።
ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ የ32 ዓመት ጣሊያናዊ በግድያ እና በስርቆት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ውሏል።
በበይነ መረብ በተሰራጩ ቪዲዮዎች ላይ አንድ ግለሰብ ኦጎርቹክዉ ላይ ተቀምጦ ተደጋጋሚ ቡጢ ሲያሳርፈበት ያሳያሉ።
በጠራራ ፀሀይ የተፈጸመውን ጥቃት ከተመለከቱት መካከል አንዳቸውም ለመገላገል አልሞከሩም።
"ይህ የማላውቀው የክፋት ዓይነት ነው” ስትል የኦጎርቹክዉ ባለቤት ቻሪቲ ኦሪያቺ ለቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ተናግራለች።
ኦሪያቺ የባለቤቷን ህልፈት ለመቀበል ድጋፍ እንዳገኘች ተናግራለች። "መናገር” እንደደከማት እና አሁን ፍትህ የማግኘት ፍላጎት ብቻ እንዳላት ገልጻለች።
ቤተሰቧ በጣሊያን ለረዥም ጊዜ መኖሩን አስታውቃ ባለቤቷ ምንም አይነት ችግር ውስጥ ገብቶ እንደማያውቅ ገልጻለች።
ግድያው በሳምንቱ መጨረሻ ወደ ጎዳና ለተቃውሞ የወጡትን ናይጄሪያውያን ጨምሮ በአካባቢው ማህበረሰብ ዘንድ ቁጣ ቀስቅሷል። ናይጄሪያዊያኑ በቅርቡ ሌላ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አቅደዋል።
የጣሊያን ባለስልጣናት “አስከፊ ወንጀል የፈፀመውን ግለሰብ በፍጥነት ለፍርድ እንዲያቀርቡ” የናይጄሪያ መንግስት ጠይቋል።
ተጠርጣሪው አልተፈታም
ምርመራው የቀጠለ ሲሆን ፊሊፖ ክላውዲዮ ጁሴፔ ፌርላዞ የተባለው ነጭ ተጠርጣሪ ግለሰብ በእስር ቤት እንዲቆይ ተወስኗል።
ጠበቃው ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት ተጠርጣሪው ይቅርታ መጠየቁን እና “በምንም መልኩ ከዘር ጋር ግንኙነት” እንደሌለው ተናግሯል።
ነጋዴው ተጠርጣሪውን እና ጓደኛውን በተደጋጋሚ መልስ በመጠየቁ ኦጎርቹክዉ ጥቃት እንደደረሰበት የፖሊስ መርማሪ አስታውቋል።
ኤሌና ዲ የተባለችው የጥቃት አድራሹ ተጠርጣሪ ጓደኛ ኦጎርቹክዉ ክንዷን እንደነካው ለጣሊያኑ ጋዜጣ ኮሪሬ ዴላ ሴራ ተናግራለች። ይህ ግን እንዳላስጨነቃትም ጨምራ አስታውቃለች።
ኦሪያቺ ባሏን ለምን እንደገደለው ለማወቅ ተጠርጣሪውን "ፊት ለፊት" ማየት ትፈልጋለች ሲሉ የቤተሰቡ ጠበቃ ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።