አውሮፕላን ሰርቆ የመገበያያ መደብር ውስጥ ለማብረር የዛተው አሜሪካዊ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Mary Ellen Rogers
አነስተኛ አውሮፕላን ሰርቆ ወደ ዋልማርት የመገበያያ መደብር ውስጥ ለማብረር የዛተው አሜሪካዊ ግለሰብ በከፍተኛ ዘረፋ እና በሽብር ዛቻ ተከሷል።
ኮሪ ዌይር ፓተርሰን በሚል በፖሊስ የተጠቀሰው ግለሰብ በቱፔሎ ሚሲሲፒ ለሰዓታት በማብረር ከተሽከረከረ በኋላ በሜዳ ላይ ሲያርፍ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ግለሰቡ በአየር ላይ እያለም ፖሊስ እያናገረው የነበረ ሲሆን በዋልማርት ውስጥ የነበሩ ተገልጋዮችም ለቀው እንዲወጡ ተደርገዋል።
ተጠርጣሪው በአካባቢው አየር ማረፊያ ውስጥ ይሠራ እንደነበር ነገር ግን የአብራሪ ፈቃድ አለው ተብሎ እንደማይታመን የከተማው ፖሊስ ተናግሯል።
ሆኖም የተወሰኑ የበረራ ትምህርቶችን እንደወሰደም ተገልጿል።
ኮሪ ፓተርሰን በቢችክራፍት ኪንግ ኤይር ኩባንያ የሚመረተው ትዊን ኢንጂን አውሮፕላን ከመብረሩ በፊት ሰርቆታል ተብሏል።አነስተኛው አውሮፕላን ከ10-11 መቀመጫ አለው።
ተጠርጣሪው አውሮፕላኑን ከሰረቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋልማርት መገበያያ መደብር ውስጥ ለመግባት እንዳሰበ ለፖሊስ በ911 ስልክ ደውሎም ተናግሯል።
የግለሰቡንም ዛቻ ተከትሎ በህንፃው እንዲሁም በአቅራቢያው ያሉ ሱቆች ውስጥ ያሉ ሰራተኞችና ተገልጋዮች እንዲወጡም ባለስልጣናቱ አደገኛ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
የአከባቢው የፖሊስ ኃላፊ ጆን ኩዋካ እንደተናገሩት ተደራዳሪዎች ፓተርሰን ልምድ ባይኖረውም ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ አውሮፕላን ማረፊያው ላይ እንዲያርፍ ማሳመን ችለዋል። በዚህም ግለሰቡ ወደ መገበያያ መደብሩ ለማብረር ይዞት የነበረው እቅድ ሳይሳካ ቀርቷል።
ተደራዳሪዎቹ ከተጠርጣሪው ጋር ስላደረጉት ውይይትም ሆነ ግለሰቡ በመገበያያ መደብሩ ላይ ማብረር ለምን እንደፈለገ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።
የበረራ ተቆጣጣሪዎች አውሮፕላኑ በከተማው ላይ እና በአካባቢው ላይ ለሰዓታት ሲያንዣብብ እየተቆጣጠሩት ነበር ተብሏል።
ብዙም ሳይቆይ የአካባቢው የቴሌቭዥን ጣቢያ ደብሊውቲቪኤ በቀጥታ ስርጭቱ አውሮፕላኑን በሜዳ ላይ ቆሞ አሳይቷል።












