በታኅሣሥ ወር ብቻ 2 ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ በየቀኑ ፌስቡክ ተጠቅሟል

ማርክ ዛከርበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማርክ ዛከርበርግ
ታትሟል

ግዙፉን የማኅበራዊ ትስስር መድረክ ፌስቡክን የሚጠቀመው የዓለም ሕዝብ ቁጥር ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ በአማካይ 2 ቢሊዮን መድረሱ ተነገረ።

ይህም ማለት ከአጠቃላዩ የምድራችን ነዋሪ ሩብ የሚሆነው ፌስቡክን መጠቀም ዕለታዊ ተግባሩ አድርጎታል ማለት ነው።

ይህ ከፍተኛ የተጠቃሚዎች ቁጥር የፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ ኩባንያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከደረሰበት የፋይናንስ ቀውስ ሊታደገው ይችላል ተብሏል።

ኩባንያው ካለፈው የፈረንጆች ዓመት ወዲህ የማስታወቂያ ገቢው እየቀነሰ ጠቅላላ ኩባንያውን ለማስተዳደር የሚያወጣው ወጪ ደግሞ እየጨመረ መጠነኛ ችግር ውስጥ ገብቶ እንደነበር ይታወሳል።

ይሁንና መሥራቹ ማርክ ዛከርበርግ “2023 ውጤታማ ዓመት ይሆናል” ብሎ መናገሩን ተከትሎ የሜታ ኩባንያ የአክሲዮን ገበያ ሽያጩ ከፍ ብሏል።

ዛከርበርግ እንደሚለው አሁን እሱና ኩባንያው ወጪ በመቀነስ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደርጋል።

ፌስቡክ ላለፉት ረዥም ዓመታት ባለ ሁለት አሐዝ የገቢ ዕድገት ሲያሳይ ቆይቶ ነው ባለፈው የፈረንጆች ዓመት መንገጫገጭ የገጠመው።

በርካታ ሠራተኞችን ቅነሳ ካደረገ በኋላ ድርጅቱ አሁን ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለነው ብሏል መሥራቹ ማርክ ዛከርበርግ።

ሜታ ኩባንያ ከፌስቡክ ሌላ ኢንስታግራምን እና ዋትስአፕን በባለቤትነት ያስተዳድራል።

ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ይህ ኩባንያ ወጪውን ለመቀየር መዋቅሩን በማስተካከል 11ሺህ ሠራተኞችን ከሥራ አሰናብቷል።

ይህም ከጠቅላላ የሠራተኛ ቁጥሩ 13 እጁን ይይዛል።

ይህ መዋቅር የማስተካከሉ ሂደት 4.5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ አስወጥቶታል። ይህም ሆኖ ባለፈው ዓመት 23.2 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ አስመዝግቧል።

ሜታ ባለፈው ዓመት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ እየቀነሰብኝ ነው ሲል ለሸሪኮቹ እንድታውቁት የሚል መልዕክት ልኮ ነበር። ይህ የተጠቃሚዎች ቁጥር መቀነስ በፌስቡክ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተ ነበር።

ይህን ተከትሎ ኩባንያው የኢንቨስትመንት ትኩረቱን ምናባዊ እውነታ (Virtual reality) ላይ እንደሚያደርግም ጠቁሞ ነበር።

ይሁንና ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ዕለታዊ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በአራት እጅ ጨምሮ ታይቷል።

ዛከርበግር እንደሚለው ኩባንያው አጫጭር ቪዲዮ የሚያጋራበት ሪል (Reel) በደንበኞቹ ዘንድ እየተወደደለት መጥቷል። ይህ በተለይ በወጣቶች ዘንድ ይበልጥ የሚመረጥ ቲክቶክን የመሰለ የማኅበራዊ ትስስር አንድ መንገድ ነው።

ይህ ከቲክቶክ ጋር የሚመሳሰለው ሪል ተጠቃሚዎችን እያበዛለት እና ዶላርም እያስገባለት እንደሆነ ኩባንያው ተናግሯል።

ሜታ ባለፉት ዓመታት መንገጫገጩን ተከትሎ ገበያ ያጡ ድርሻዎችን ከድርሻ ገበያ 40 ቢሊዮን ዶላር አውጥቶ መልሶ እንደሚገዛቸውም አስታውቋል።