ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳ ለህወሓት ኃይሎች ሥልጠና እና ድጋፍ ትሰጣለች የሚለውን ክስ አስተባበለች
የኡጋንዳ ሠራዊት የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) አባላትን በማሰልጠን ኢትዮጵያን ለማናጋት እየሰራ ነው የሚለውን ክስ አስተባበለ።
ከአንድ ዓመት በፊት አንስቶ ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ጋር ጦርነት ውስጥ የገባውን ህወሓትን የኡጋንዳ ሠራዊት ሥልጠና እና ሌሎች ድጋፎችን እየሰጠ ነው የሚሉ ዘገባዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ነው ምላሹ የወጣው።
ይህ ኡጋንዳ ለህወሓት ድጋፍ እያደረገች ነው የሚለው ዘገባ በኢትዮጵያውያን የበይነ መረብ ገጾች ላይ ካለፈው ግንቦት ወር ወዲህ በመውጣት መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል።
የኡጋንዳ ጦር ሠራዊት ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ፌሌክስ ኩላዬጊዬ እሁድ ዕለት በሠራዊታቸው ላይ የቀረበውን ክስ በማስመልከት በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፣ ኡጋንዳ የኢትዮጵያን ሰላም ለማናጋት ጥረት እያደረገች ነው የሚለው ክስ ፍጽም ፈጠራ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ይህንን ክስ የተመለከተው ዝርዝር ጽሁፉ መቀመጫው ኒውዚላንድ በሆነ የበይነ መረብ ገጽ ላይ ባለፈው የወጣ ሲሆን፣ ጽሁፉ ህወሓትን በተመለከተ የሚካሄደውን ሥራ የሚያስተባብሩ ናቸው የተባሉ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና ሌሎች የደኅንነት ኃይሎች አባላትን ስም ዝርዝር ይዟል።
ሥልጠናውም በማዕከላዊ ኡጋንዳ ክፍል ውስጥ በሚገኘው ማሳካ ወረዳ ውስጥ እንደሚካሄድ ገልጾ ነበር።
የወጣው ሰነድ ጨምሮ እንደሚያመለክተው ከ4,000 በላይ የህወሓት ተዋጊዎች ኡጋንዳ ውስጥ በሚገኙ በአራት የማሰልጠኛ ጣቢያዎች ውስጥ ለወታደራዊ ሥልጠና መግባታቸውን አመልክቷል።
ከዚህ ባሻገር ይህ ሥልጠና ኡጋንዳ ውስጥ ይካሄድ እንጂ በአሜሪካ እና በግብፅ የሚደገፍ መሆኑንም በሰነዱ ላይ ተገልጿል።
በዘገባው ላይ ስማቸው ከተጠቀሱት የኡጋንዳ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መካከልም የፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ልጅ እና የአገሪቱ የምድር ጦር ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል ሙሁዚ ኪያኔሩጋባ ይገኙበታል።
ጄኔራሉ በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ውስጥ ጦርነቱ በተቀሰቀሰበት ጊዜ በትዊተር ገጻቸው ላይ የትግራይ ኃይሎችን “ወንድሞች” በማለት ድጋፋቸውን ገልጸው ነበር።
የትግራይ ኃይሎች ከኡጋንዳ ድጋፍ ያገኛሉ የሚለው ሰነድ ትክክለኛ ይሁን ወይም የሐሰተኛ ዜና ዘመቻ አካል ስለመሆን አለመሆኑ እስካሁን ግልጽ አይደለም።
‘ስኩፕ’ የተባለውና ሰነዱን ይፋ ያደረገው በኒውዚላንድ የሚገኘው በይነ መረብ የሰነዱን ምንጭ እንዲሁም የይዘቱን ዝርዝር ትክክለኛነት ለማረጋገጥ እንዳልቻለ ገልጿል።
ነገር ግን በሰነዱ ላይ አንዳንድ ትክክል ያልሆኑ ነገሮች መኖራቸው ተገልጿል።ሰነዱ የኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ብሎ የሚጠቅሳቸው ጄምስ ካባሬቤ የሚል ሲሆን፣ የተጠቀሰው ስም ያላቸው ግለሰብ በዚህ የሥልጣን ቦታ ላይ ፈጽሞ አልነበሩም ተብሏል።
የኡጋንዳ ጦር ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ፌሌክስ ኩላዬጊዬ፣ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ኡጋንዳና ደቡብ ሱዳን በጋራ እየሰሩ ነው የሚለው ክስም ሐሰት ነው ብለዋል። በሰነዱ ላይ በደቡብ ሱዳን የኡጋንዳ አምባሳደር በአስተባባሪነት የተጠቀሱ ሲሆን፣ አምባሳደሩ ከተጠቀሱት የደቡብ ሱዳን ጄኔራል ጋር ፈጽሞ ተገናኝተው እንደማያውቁ አስተባብለዋል።
ኡጋንዳ በምሥራቅ እና በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በሚኖሩ ግጭቶች ውስጥ የመሳተፍ ታሪክ እንዳላት ይነገራል። ሠራዊቷ በአሁኑ ጊዜ በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ከአገሯ አማጺያን ጋር እየተዋጋ ይገኛል።
የአፍሪካ ኅብረት አልሻባብን ለመዋጋት ወታደራዊ ኃይል ወደ ሶማሊያ ሲያሰማራ ኡጋንዳ ሠራዊቷን የላከች ቀዳሚዋ አገር ናት።
በተጨማሪም ከዓመታት በፊት የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪር ከምክትላቸው ጋር ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ግጭት ሲከሰት፣ ኡጋንዳ ሠራዊቷን በመላክ ከፕሬዝዳንቱ ጎን ተሰልፋ ነበር።
ከአስር ዓመት በፊትም የኡጋንዳ ሠራዊት በምሥራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ ውስጥ ከሩዋንዳ ሠራዊት ጋር ተጋጭቶ እንደነበር ይታወሳል።