ካማላ ሃሪስ የጋዛ ጦርነት ማብቂያ ‘ጊዜው አሁን ነው’ ሲሉ ለኔታኒያሁ ተናገሩ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ።
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት እና በቀጣዩ ምርጫ የዲሞክራቶች ዕጩ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ካማላ ሃሪስ ከእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ጋር “ቀጥተኛ እና ገንቢ” ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ።

እስራኤልን በተመለከተ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለዘብተኛ ንግግር በተለየ መልኩ ካማላ ሃሪስ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እያደረሰ ያለው ጉዳት “እጅጉን ያስስበኛል” ሲሉ ጠንከር ያለ አስተያየት ሰጥተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ ጋር በነበራቸው ውይይት ምክትል ፕሬዝዳንት ሃሪስ የጋዛ ጦርነት ማብቂያ ‘ጊዜው አሁን ነው’ ብለዋል።

ሃሪስ ለአስርት ዓመታት የዘለቀውን የእስራኤል እና ፍልስጤማውያን ውዝግብ ለመፍታት የሁለት አገር አማራጭንም ወደፊት አምጥተዋል።

ኔታኒያሁ ከምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ጋር በዋይት ሃውስ የተገናኙት ከአንድ ቀን በፊት በአሜሪካ ኮንግረስ ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።

ኔታኒያሁ በኮንግረሱ ሐማስ ላይ “ሙሉ ድል” እንጎናጸፋለን የሚል ንግግራቸውን ሲያሰሙ የፍልስጤም ደጋፊዎች ከጎንግረሱ ፊት ለፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲቃወሙ ነበር።

ዘጠኝ ወራትን ያስቆጠረው የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት እንዲያበቃ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ኔታኒያሁ ትልቅ ጫና ውስጥ ይገኛሉ።

ካማላ ከኔታኒያሁ ጋር በነበራቸው ውይይት የጋዛ ጦርነት እያስከተላቸው ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እጅጉን አሳስቦኛል ይበሉ እንጂ፤ እስራኤል እራሷን ለመከላከል ለምታደርገው ጥረት የአሜሪካ “የማይቋረጥ ድጋፍ” አይለያትም ብለዋል።

የእስራኤል-ጋዛ ጦርነት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. የሐማስን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ መጀመሩ ይታወሳል። በዕለቱ ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር ዘልቆ 1200 ሰዎችን ገድሎ ከ250 ያላነሱ ሰዎችን አግቶ መውሰዱ ይታወሳል።

እስራኤል እየወሰደች ባለችው የአጸፋ ምላሽ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑት ከ39ሺህ በላይ ሰዎችን ከመግደሏ በተጨማሪ የጋዛ ሰርጥን አውድማለች።

ካማላ በኔታኒያሁ ጋር በነበራቸው ውይይት “እስራኤል እራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ሁሉ እራሷን እንዴት መከላከል አለባት የሚለውም ወሳኝ ነው” ብለዋል።

በጋዛ ስላለው “የከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ ዝም ማለት አልችልም” ብለዋል።

“የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ እናድርግ። . . . ታጋቾችን እናስለቅቅ፤ ለፍልስጤማውያን እረፍት እንስጣቸው” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ በአሜሪካ የሚያደርጉት ጉብኝት ቀጥለው ዛሬ አርብ ከሪፓብሊካን ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ይገናኛሉ ተብሏል።