ሪፐብሊካኑ የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት ለካማላ ሐሪስ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ ገለጹ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የቀድሞው የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት እና የሪፐብሊካን አባል የሆኑት ዲክ ቼኒ ድምጻቸውን ለዲሞክራቷ ካማላ ሐሪስ እንደሚሰጡ አስታወቁ።

ዲክ ቼኒ በፕሬዝዳንት ጆርጅ ደብሊው ቡሽ የሥልጣን ዘመን ተጽዕኖ ፈጣሪ የነበሩ ሲሆን ውሳኔያቸውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ላይ "ከዶናልድ ትራምፕ የበለጠ ለሪፐብሊካችን አደገኛ የሆነ ግለሰብ የለም" በማለት ተናግረዋል።

ሊዝ ቼኒ፣ የዲክ ቼኒ ሴት ልጅ፣ በዚህ ዓመት የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አባቷ ከዲሞክራቷ ካማላ ሐሪስ ጎን መቆማቸውን ተናግራለች።

"ምንም እንኳ መራጮች ድምጽ ቢነፍጉትም፣ትራምፕ የባለፈውን ምርጫ ውሸት እና አመጽን ተጠቅሞ ሥልጣን ላይ ለመቆየት በማሰብ ሊያጭበረብር ሞከሯል" ብላለች።

"ዳግም ሥልጣን ቢይዝ እምነት የሚጣልበት አይደለም" ስትልም አክላለች።

ዲክ ቼኒ "ድምፄን ለምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ እሰጣለሁ" ካሉ በኋላ "እንደ አንድ ዜጋ ሕገ መንግሥታችንን ለመከላከል ወገንተኛ ከመሆን ይልቅ አገራችንን ማስቀደም አለብን" ብለዋል።

ይህ የዲክ ቼኒ አቋም በካማላ ሐሪስ ደጋፊዎች ዘንድ ከፍተኛ ደስታን ፈጥሯል።

"ምክትል ፕሬዝዳንት፣ የምክትል ፕሬዝዳንት ዲክ ቼኒን ድጋፍ በማግኘታቸው ደስተኛ ናቸው። በተጨማሪም አገራቸውን ከፓርቲያቸው በማስቀደማቸው ከፍተኛ ክብር አለን" ብለዋል የምርጫ ዘመቻውን በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ጄን ኦማሌ ዲሎን።

ዲክ ቼኒ በሪፐብልካኑ ዶናልድ ትራምፕ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ እና ቅሬታ ሲገልጹ የመጀመርያው ሪፐብሊካን አይደሉም።

ልጃቸው ሊዝ ቼኒም ለካማላ ሐሪስ ድጋፏን ቀድማ ሰጥታ ነበር።

ይህንን የዲክ ቼኒን አቋም ከሰሙ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ የቀድሞውን ምክትል ፕሬዝዳንት "ረብ የለሽ፣ የሥም ሪፐብሊካን" ሲሉ አጣጥለዋቸዋል።

አክለውም ዲክ ቼኒን "ማለቂያ የሌለው እና ረብየለሽ ጦርነት ንጉሥ ሲሉ" በኢራቅ ጦርነት ወቅት የነበራቸውን ውግንና አመልከተው ተችተዋል።