በይርጋጨፌ ነባር የሙስሊም መካነ መቃብር በኮሪደር ልማት ይፈርሳል መባሉ ቅሬታ ገጠመው

ይርጋ ጨፌ

የፎቶው ባለመብት, YIRGACHFIE COMM.

የምስሉ መግለጫ, ይርጋጨፌ ከተማ
ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጌዲዮ ዞን፣ ይርጋጨፌ ከተማ ነባር የሆነ የሙስሊም መካነ መቃብር የተወሰነ ክፍሉ ለኮሪደር ልማት ይፈርሳል መባሉ ቅሬታ መፍጠሩን ነዋሪዎች እና የከተማው የእስልምና ጉዳዮች ሰብሳቢ ተናገሩ።

በከተማው የሚገኘው የቢላል መካነ መቃብር የመንገድ ማስፋፊያን ጨምሮ “ለሕዝብ መዝናኛ” ግንባታ 15 ሜትሩ እንደሚፈልግ የከተማው አስተዳደር ማሳወቁን ተናግረዋል።

መንገድ ዳር የሚገኘው እና ለ50 ዓመታት ዘላቂ ማረፊያ የሆነው መካነ መቃብሩ ለመንገድ ማስፋፊያ የተፈለገውን አምስት ሜትር ገደማ “አገራዊ ነው” በማለት ለኮሪደር ልማቱ እንዲውል ይሁንታ ቢያገኝም፤ ተጨማሪ የመካነ መቃብሩን 10 ሜትር መፈለጉ ግን ተቃውሞ ገጥሞታል።

የከተማው አስተዳደር በይርጋጨፊ ከሚገነቡ አራት ዘላቂ ማረፊያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን ጠቅሶ ‘ልማቱ አይቀሬ ነው’ ብሏል።

አንድ ለጉዳዩ ቀረብ ያሉ የአካባቢው ነዋሪ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ “ከሚፈለገው በላይ” አንሰጥም እያለ ነው በማለት፤ ቅራኔው ለመዝናኛ ከተባለው ተጨማሪ ክፍል ጋር የተያያዘ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የይርጋጨፌ እስልምና ጉዳዮች ዋና ሰብሳቢ ሃጂ ጀማል ዳሪ በሕዝበ ሙስሊሙ እና በአካባቢው አስተዳደር መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ገልጸው፤ የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል።

“[ማኅበረሰቡ] ‘15 ሜትር ሲገባ ብዙ መቃብር ያስነሳል፤ በመንገድ ልክ [አምስት ሜትር ማስፋፊያ] እንሰጣለን። ከዚያ በተረፈ ተጨማሪ የተባለው ነገር ይቀየርልን የሚል ጥያቄ በቃልም በደብዳቤም አሳወቀ’” ሲሉ ይህንም ሕዝቡ የወከላቸው የኮሚቴ አባላት “ተመላልሰው” አሳውቀዋል ብለዋል።

“[መንግሥት] ልኬቱ አይቀየርም በሚል ደምድሞ ዘጋ። ለሕዝቡ ወርዳችሁ ይህን አሳምኑ የሚል በተደጋጋሚ የቤት ሥራ ተሰጥቶን ወደ ሕዝቡ ስንሄድ ደግሞ፤ ‘ከመንገድ ልኬት ውጪ እኛ አንፈቅድም’ የሚል አንድ አቋም ይዟል። እስከ ዞን ድረስ ለሚመለከተው መሥሪያ ቤት አሳውቀናል” ሲሉ የተፈጠረውን ልዩነት ገልጸዋል።

ከመካነ መቃብሩ የሚፈለገው ስፍራ “ፋውንቴን፣ ማረፊያዎች፣ መዝናኛ፣ በጎን ሱቆች” እንደሚሠሩበት መነገሩን ለጉዳዩ ቀረብ ያሉ ነዋሪ ተናግረዋል።

“ትላልቅ መሻይኮች እና ኡለማዎች ያረፉበት ቦታ ነው። መካነ መቃብር በእኛ ክብር አለው። በእምነቱ አይደለም ሌላ ህንጻ [መገንባት] መርገጥ በራሱ በጣም ክልክል ነው” ሲሉ ማኅበረሰቡ ከመካነ መቃብሩ ጋር ያለውን ቁርኝት ገልጸዋል።

ሃጂ ጀማል ‘ለመዝናኛ እና ማረፊያ’ የተፈለገው የመካነ መቃብሩ ክፍል “ብዙ መቃብር የሚያስነሳ ነው። በእኛ አቅምም የሚቻል አይደለም” በሚል ፕላኑ እንዲቀየር ሕዝቡ መጠየቁን ተናግረዋል።

የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ታደለ ጥላሁን ግን ለአምስት ጊዜ ያህል ስብሰባ አድርገው መቃብሩን ለማንሳት ስምምነት ተደርሶ እንደነበር ጠቅሰው፤ በ10 ቀናት ውስጥ አጽም ወደ ዘላቂ ማረፊያ እንዲዘዋወር ተስማምተናል ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ከከተማው አስተዳደር “ፕላኑ መቀየር አይችልም” በሚል መልስ እንደተሰጣቸው የጠቆሙት ዋና ሰብሳቢው ደግሞ መግባባት ላይ ሳይደረስ ረቡዕ ኅዳር 4/2015 ዓ.ም. የመካነ መቃብር አጥር እንደፈረሰ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም አካባቢው ላይ ግርግር ተፈጥሮ ነበር ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አጥሩ ሲፈርስ “ሕዝቡ በነቂስ ወጣ” ያሉት ዋና ሰብሳቢው፤ በተለይም በአካባቢው ቤታቸው የፈረሰባቸው እና በመካነ መቃብሩ ቤተሰቦች ያሏቸው ሰዎች “በቁጣ” ወጥተው እንደነበር ገልጸዋል።

ከንቲባው በበኩላቸው “ፕሮጄክቱን ወደ መሬት ማውረድ ስለተፈለገ በፍጥነት አንሱ [ተባሉ] በዚያ ጊዜ ማንሳት አልቻሉም። እኛ ከታች ያለውን አጥሩን ለማንሳት ስንሄድ የተወሰነ አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር” ብለዋል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ የመካነ መቃብሩ አጥር ሲፈርስ በማኅበረሰቡ እና በፖሊስ መካከል “ግርግር” መፈጠሩንም ገልጸው፤ 14 ወጣቶች መታሰራቸውን ተናግረዋል።

የማኅበረሰቡ ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ “ተረበሸ” ያሉት ሃጂ ጀማል በበኩላቸው፤ በግርግሩ ሰዎች መታሰራቸውን አረጋግጠዋል።

ማኅበረሰቡ እንዲረጋጋ ማድረጋቸውንም ገልጸው ከከተማው አስተዳደር ጋር ውይይት ተደርጎ የታሰሩት ወጣቶች ማታ 2፡30 ገደማ ከአንድ ሰው በስተቀር እንዲፈቱ መደረጉን ተናግረዋል።

ከታሳሪዎቹ መካከል አንዱ ወጣት “ሁከት የመፍጠር አዝማሚያ እና ቅስቀሳ አድርገሃል፤ ቪዲዮም ቀርጸሃል” በሚል እንዳልተፈታ አንድ ነዋሪ ተናግረዋል።

የይርጋጨፌ ሕዝበ ሙስሊም ይሠራል የሚባለው የሕዝብ መዝናኛ ስፍራ ከመካነ መቃብሩ ጋር አይጣጣምም የሚል ስጋትም እንዳላቸው ሃጂ ጀማል ገልጸዋል።

“[መዝናኛው] ከመካነ መቃብሩ እና ከመስጊዱ [ጋር] አብሮ አይሄድም። ቦታው ወደ ልማት [የመስጊድ ማስፋፊያ] ቢውል ከፊት ለፊቱ ተጨማሪ ነገር ካለ አይመችም” የሚል ስጋት እንደነገሰም ተናግረዋል።

ሕዝቡን የወከለው ኮሚቴ አባል የሆኑ አንድ ግለሰብ “የመዝናኛ ቦታ መካነ መቃብር ላይ አይሆንም። የእምነቱም ሥርዓት አይፈቅድም” ሲሉ የተቃውሞውን ተጨማሪ ምክንያት ተናግረዋል።

ሕዝበ ሙስሊሙ እስላማዊ ሥርዓትን ተከትሎ በኡለማዎች ፈቃድ “ወሳኝ” የተባለውን የቢላል መስጊድ የማልማት ፍላጎት እንዳለው ሃጂ ጀማል ገልጸዋል።

የከተማው ከንቲባ አቶ ታደለ መካነ መቃብሩ አስፓልት ዳር የሚገኝ “ዓይን” ቦታ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ ቀደምም በሚነሳበት ጉዳይ ዙሪያ ንግግሮች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ከንቲባው ተቃውሞው ከአብዛኛው የሙስሊም ማኅበረሰብ ሳይሆን ልማቱን በተሳሳተ መልኩ እንዲታይ የሚያደርጉ “የጥቂት ጽንፈኞች አጀንዳ” ነው ብለው ያምናሉ።

“የግለሰብ ቤቶችም ፈርሰዋል። የመንግሥት ተቋማት ፈርሰዋል። የሌላ ሃይማኖት የፈረሰበት አለ። አገራዊ አጀንዳ [ነው]፤ ፕላን የማስጠበቅ ጉዳይ ነው። ፕላን የማስጠበቅ ጉዳይ ለየትኛውም ድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም” ሲሉ የአስተዳደራቸው እርምጃ እንደሚጸና ተናግረዋል።

የከተማው አስተዳደር እስከ እሁድ ኅዳር 8 ድረስ አንስታችሁ አስረክቡኝ ማለቱን ያሳወቁት የከተማው እስልምና ጉዳዮች ዋና ሰብሳቢው፤ በዕለቱ የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ ስብስባ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የሕዝቡን ውሳኔ በማግስቱ ሰኞ ለከተማው አስተዳደር እንደሚያሳውቁ ሃጂ ጀማል ተናግረዋል።

የቢላል መካነ መቃብር ከአጠገቡ አነስተኛ መስጊድ የያዘ እና በመሙላቱ ምክንያት የቀብር አገልግሎት መስጠት አቁሟል ብለዋል።