በአሜሪካ የካናቢስ እርሻ ውስጥ አራት ቻይናውያንን እንደገደለ የተጠረጠረው ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, CBS
ባለፈው ዕሁድ በአሜሪካ ኦክላሆማ ግዛት በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ ባለ የማሪዋና (ሃሽሽ) እርሻ ላይ የሚሰሩ አራት የቻይና ዜግነት ያላቸውን ሰዎች እንደገደለ የተጠረጠረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን መርማሪዎች አሳወቁ።
ዉ ቼን የተባለው የ45 ዓመቱ ተጠርጣሪ ወንጀሉ ከተፈጸመበት 2 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ፍሎሪዳ ግዛት በቁጥጥር ስር መዋሉም ተጠቁሟል።
የሟቾቹ አስክሬንም እገታ በሚመስል መልኩ ለፖሊስ በተደረገው ጥሪ ከኦክላሆማ ከተማ በ88 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ሄንሲ በተባለች አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነው የተገኘው።
ኦክላሆማ ለመድኃኒትነት የሚውሉ የካናቢስ እርሻዎችን የምትፈቅድ ሲሆን፣ ቻይናውያኑ የተገደሉበት እርሻ ግን ፍቃድ ይኑረው አይኑረው የታወቀ ነገር የለም።
ተጠርጣሪው ባለፈው ዕሁድ ወደ የማሪዋና እርሻው ወደሚመረትበት ህንጻ በርካታ ሠራተኞች ባሉበት ሰዓት ዘልቆ መግባቱን ፖሊስ ገልጿል።
ግድያውን ከመፈጸሙ በፊት ህንጻው ውስጥም ዘለግ ላለ ሰዓታት መቆየቱን የኦክላሆማ ወንጀል ምርምራ ቢሮ አስታውቋል።
10 ሄክታር በሚሸፍነው የእርሻ ቦታ ላይ የተገደሉት ሦስት ወንዶች እና አንዲት ሴት ናቸው።
ሌላ የቻይና ዜግነት ያለው ግለሰብም ባልተገለጸ የጉዳት መጠን ሆስፒታል ገብቷል።
“በከፍተኛ የቋንቋ ችግር” ሳቢያ ለተጎጂ ቤተሰቦች እስካሁን መረጃ እንዳልተሰጠም ፖሊስ ገልጿል።
ተጠርጣሪው ትናንት ማክሰኞ የተሽከርካሪው የሰሌዳ ቁጥር በዘመናዊ መቆጣጠሪያ ከተለየ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ዜግነቱ ያልተገለጸው ተጠርጣሪው ላለመያዝ ምንም አይነት መከላከል ሳያደርግ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ለኦክላሆማ ፖሊስ ተላልፎ እስኪሰጥ እየጠበቀ ይገኛል። ተኩሶ መግደልን ጨምሮ የተለያየ ክስም ተመስርቶበታል።
ፖሊስ ግድያው ድንገት የተፈጠረ አይመስልም ያለ ሲሆን፣ ከሟቾች ጋር ትውውቅ ሳይኖረው አይቀርም ብሏል።
የኦክላሆማ ግዛት የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ስታን ፍሎረንስ ለአሶሼትድ ፕሬስ በሰጡት አስተያየት “ዝምድና ይኑራቸው ወይም የሥራ ባልደረባ ይሁኑ የሚታወቅ ነገር የለም። ሆኖም እነዚህ ሰዎች እርስ በእርሳቸው እንደሚተዋወቁ እናምናለን” ብለዋል።
ግድያው የተፈጸመበት አካባቢ አስተዳደር በጉዳዩ ላይ የኦክላሆማ ግዛት እርዳታን ከጠየቁ በኋላ የግዛቲቱ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ተሳትፎበታል።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 በተሰጠ ደምጽ ለህክምና የሚውል የማሪዋና ልማት በኦክላሆማ ግዛት ሕጋዊ መሆኑን ተከትሎ ኢንደስትሪው በከፍተኛ ደረጃ አድጓል።
በመጪው የካቲት የኦክላሆማ ድምጽ ሰጪዎች ማሪዋና ለመዝናናት ዓላማ ይዋል ወይስ አይዋል በሚለው ጉዳይ ድምጽ ይሰጣሉ።
21 የአሜሪካ ግዛቶች ካናቢስ ለመዝናናት ጥቅም ላይ እንዲውል የፈቀዱ ሲሆን፣ 37 ግዛቶች ደግሞ ዕጹ ለመድኃኒትነት እንዲውል ይሁንታን ሰጥተዋል።












