የቻይና አረጋውያን ለጤና የሚሰጣቸው ጥቅማጥቅም በመቀነሱ ለተቃውሞ አደባባይ ወጡ

በቻይና የሚገኙ በርካታ ጡረተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በቻይና የሚገኙ በርካታ ጡረተኞች ለህክምና የሚሰጣቸው ጥቅማ ጥቅም በመቀነሱ የአደባባይ ተቃውሞ አደረጉ።

አረጋውያኑ ለሁለተኛ ጊዜ በውሃን እንዲሁም በሰሜን ምስራቅ ዳሊያን ከተሞች ተሰብስበው ታይተዋል።

የአደባባይ ተቃውሞው በሰባት ቀናት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተካሂዷል።

ተቃውሞው ገዢው ፓርቲ አመታዊውን ጉባኤውን ለማድረግና አዲስ አመራሮችን ለመምረጥ ባቀደበት ሳምንታት በፊትመደረጉ ጋር ተያይዞ በፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አስተዳደር ላይ ጫና ያሳድራል ተብሏል።

የመጀመሪያው ተቃውሞ የተደረገው ከሳምንት በፊት በውሃን ነበር።

የግዛቲቱ ባለስልጣናት ለመንግሥት ጡረተኞች የሚሰጠውን የህክምና ወጪ እንቀንሳለን ማለታቸውን ተከትሎም ነበር ከሳምንት በፊት የመጀመሪያው ተቃውሞ የተካሄደው ።

በአደባባይ ተቃውሟቸውን ያሰሙት በአብዛኛዎቹ አረጋውያን ጡረተኞች መሆናቸውን በማህበራዊ ትሰስር ገጾች የወጡ ቪዲዮዎች ያሳያል።

በርካቶችም የህክምና ወጪ ጣራ በነካበት ወቅት መንግሥት ይህንን ለማድረግ ማቀዱ እንዳስቆጣቸውም ተነግሯል።

ምንም እንኳን የጤና መድህን ጉዳዮችን የሚያዩት ክልሎች ወይም ግዛቶች ቢሆንም ተቃሞው ወደተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች ተዛምቷል። ይህም የአደባባይ ተቃውሞ እምብዛም በማይደረግባት ቻይና ላይ እንደ አዲስ ማንሰራራቱን አሳይ ነው።

ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ወጣቶች የመንግሥትን የዜሮ ኮቪድን ፖሊሲን ለመቃወም መውጣታቸው ይታወሳል። ፖሊሲው ድንገተኛና የጅምላ ምርመራ እንዲሁም የእንቅስቃሴ ገደብን ተግባራዊ ያደረገ ሲሆን በተቃውሞውም ምክንያት እንዲቀር ተደርጓል።

ነገር ግን በፖሊሲው ላይ የተደረገው ድንገተኛ ለውጥ ኮሮናቫይረስ በፍጥነት እንዲስፋፋ ምክንያት በመሆኑም በህክምና ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና አስከትሏል ተብሏል።

ቁጥራቸው ያልተገለጸ በርካታ ሰዎችም ሞት ምክንያት እንደሆነ የቢቢሲ ዘገባ የሚያመለክት ሲሆን ከሟቾቹም መካከል አብዛኞቹ አረጋውያን ናቸው።

ባለስልጣናቱ ማሻሻያ ነው በሚል የገለጹት ለጡረቶች የሚደረገው የጤና ጥቅማጥቅም ለውጥ ቻይና ከዚህ አስከፊ የኮቪድ ማዕበል መውጣቷን ተከትሎ ነው።