ሩሲያ የዩክሬንን አንድ አምስተኛ መሬት መያዟን ዜሌንስኪ ተናገሩ

የሩሲያ ወታደር በማሪዮፖል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሩሲያ ወታደር በማሪዮፖል
ታትሟል

የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ኃይል የአገራቸውን 20 በመቶ መሬት ተቆጣጥሮ መያዙን ተናገሩ።

ሉክዘምበርግ ውስጥ ላሉ የምክር ቤት አባላት ባደረጉት ንግግር ጦርነት እየተካሄደበት ያለው ግንባር ከ1 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ሰፍቷል ሲሉ ተናግረዋል።

“ለጦርነት ዝግጁ የሆነ የሩሲያ ጦር በሙሉ በዚህ ወረራ ተሳታፊ ሆኗል” ሲሉ ሉክዘምበርግ የምክር ቤት አባላት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ተናግረዋል።

የሩሲያ ኃይሎች በዶንባሳ ግዛት የምትገኘውን ሴቬሮዶንስክ ከተማን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥቃት ከፍተዋል።

የዩናትድ ኪንግደም መከላከያ ኃላፊዎች ሩሲያ በርካታ የጦር አባላት እና ተተኳሾችን በዚህ ግንባር በማሰለፏ አብዛኛውን የከተማዋን ቦታዎች መያዝ ችላለች ብለዋል።  

ሴቬሮዶንስክ በዶንባስ ግዛት የምትገኘው የመጨረሻዋ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ያለች ምስራቃዊት ከተማ ናት።

ሩሲያ ይህችን ከተማ ለመያዝ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት መክፈቷን ዩክሬናዊው የአካባቢው ገዢ ሴርሂይ ሃኢዳኢ ተናግረዋል።

የአካባቢው ገዢ የዩክሬን ወታደሮች የሩሲያን የወደፊት ግስጋሴ ለመግታት መልሶ ማጥቃት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

“የዩክሬን ወታደሮች ባካሄዷቸው የመልሶ ማጥቃት እርምጃዎች የጠላት ኃይልን ከአንዳንድ አውራ ጎዳናዎች እንዲያፈገፍጉ ማድረግ ችለዋል። ብዙ ወታደሮችም ተማርከዋል” ብለዋል።

ከፍተኛ ውጊያ እያስተናገደች በምትገኘው ሴቬሮዶንስክ ከተማ ከ15 ሺህ ያላነሱ ንፁሃን መውጫ አጥተው በከተማዋ እንደሚገኙ ተገልጿል።

በተያያዘ ዜና በደቡባዊ  ዩክሬን የምትገኘው እና በሩሲያ ቁጥጥር ሥር ባለችው ማሪዮፖል ንሑሃን ዜጎች በሩሲያ ወታደሮች መገደላቸው ተገልጿል።

የከተማዋ ከንቲባ በሞስኮ ከተሰየመው አስተዳደር ጋር አንተባብርም ያሉ የከተማ የመንግሥት ሰራተኞች በሩሲያ ጦር እየተገደሉ ነው ሲሉ ክስ አሰምተዋል።

ከተማዋ በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ስር ከመውደቋ በፊት ከከተማዋ የመወጡት ከንቲባ ቫደይመ ቦይቼንኮ በርካታ ሰዎች በሩሲያ ጦር ቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ እና ስቃይ የሚደርስባቸውም ስለመኖራቸው ተናግረዋል።

ከንቲባው ባለፈው ሳምንት የሩሲያ ጦር ከተማዋን ለመያዝ ከፍቶት በነበረው ጥቃት ከ22ሺህ በላይ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረው ነበር።