የሩሲያ አዲስ የወታደር ምልመላ በዩክሬኑ ጦርነት ለውጥ አያመጣም ተባለ  

russia

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ዩናይትድ ኪንግደም ሩሲያ እያካሄደችው ያለው አዲስ የወታደር ምልመላ በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ለውጥ አያመጣም አለች።

ሩሲያ የጦር ኃይሏን ለማስፋት በማቀድ የጀመረችው አዲስ ምልመላ፣ በዩክሬን ጦርነት ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል ተብሎ እንደማይታሰብ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መከላከያ ሚኒስቴር ገልጿል።

በቅርቡ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ ሠራዊት ቁጥር በ137 ሺህ በመጨመር ወደ 1.15 ሚሊዮን ከፍ እንዲል የሚያስችል ሕግ ፈርመው አጽድቀዋል።

ፑቲን አዋጁን ያጸደቁት ለወታደራዊ ምልመላ ቅስቀሳ ማደረግ ከተጀመረ በኋላ ነው።

ይሁን እንጂ የዩኬ የመከላከያ ሚኒስቴር የሩሲያ ሠራዊት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ብዙ እልቂት እያጋጠመው መሆኑ አዲስ ምልምል የውጊያ አቅምን የመጨመር ዕድሉ አናሳ ነው ይላል።

መልማዮች ወደ እስር ቤቶች ጨምር በመሄድ ለታራሚዎች ከእስር እንደሚለቀቁ እንዲሁም ገንዘብ እንደሚሰጣቸው በመግለጽ ለምልመላ እያግባቡ እንደሚገኙም ዘገባዎች ጠቁመዋል።

ሩሲያ በአሁን ወቅት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወታደሮች እና 900,000 የሚጠጉ ሲቪል ሠራተኞች አላት።

የዩናይት ኪንግደም መንግሥት በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ላይ በሚሰጠው መደበኛ መግለጫዎች በአንዱ ላይ፤ በሩሲያ የታቀደው ምልመላ በፈቃዳቸው የሚመዘገቡ ሰዎችን በመመልመል ይሟላል ወጥስ የግዳጅ ምልመላ ማድረግ ያስፈልግ እንደሆነ ግልፅ አይደለም ብሏል።

ነገር ግን የሠራዊት ቁጥር ጭማሪው በየትኛውም መንገድ ይካሄድ በዩክሬኑ ጦርነት ላይ ተጽእኖ የመፍጠር ዕድሉ አነስተኛ ነው ሲል የዩኬ መንግሥት ገልጿል።

ከእነዚህ ምክንያቶች መካከል አንዱ ሩሲያ በዩክሬኑ ጦርነት በርካታ ወታደሮቿን ማጣቷ ይገኝበታል።

ምዕራባዊያኑ ሩሲያ ከስድስት ወራት በፊት ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ከ70 እስከ 80 ሺህ የሚጠጉ ወታደሮቿ ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ሲሉ ይገልጻሉ።

ሩሲያ በየካቲት ወር ዩክሬንን ሰትወር አጭር ወታደራዊ ዘመቻ አቅዳ የነበረ ቢሆንም፣ በዩክሬን ምከታ ግስጋሴዋ እንዳታቀደው አልሆነም።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታትም በተለያዩ ግንባሮች ጦርነቱ ይሄ ነው የሚባል እንቅስቃሴ ሳያሳይ ቆይቷል።

በሩሲያ ከ18 እስከ 27 ዓመት የሆናቸው ወንድ የአገሪቱ ዜጎች የውትድርና አገልግሎት ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን በጤና ምክንያቶች ወይም ከፍተኛ ትምህርትን የሚቀላቀሉ ከሆነ ግን ከዚህ ግዳጅ ነጻ ይሆናሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ዩክሬን የሩሲያ ወታደሮች ዛፖሪዢያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ቅጥር ግቢን በድጋሚ እየደበደቡ ነው ስትል ከሳለች።

የፋብሪካው ተቆጣጣሪዎች ሚሳኤሎች ከኃይል ማመንጫዎቹ አጠገብ የሚገኘውን የነዳጅ ማከማቻ የሚመቱ ከሆነ ጨረሩ በአካባቢው ሊያፈተልክ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

አክለውም የጣቢያው መሠረተ ልማቶች ላይ በደረሱ ጉዳቶች አማካኝነት የሃይድሮጂን መፍሰስ እና የራዲዮአክቲቭ ንጥረ ነገሮች የማፈትለክ አደጋዎች መጋረጣቸውን ተናግረዋል።