ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በጭስ ‘በታፈኑት' የአሜሪካ ከተሞች በርካታ የአየር ጉዞዎችና መርሃ ግብሮች ተሰረዙ
በካናዳ ተቀስቅሶ ሚሊዮኖች ላይ ተጸህኖ እያሳደር ያለው የሰደድ እሳት በአሜሪካ ከተሞች ዋሽንግተን ዲሲና ፊላዴልፊያ ከተሞች ያለው የአየር ጥራት በዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ እንዲያሽቆለቁል ምክንያት ሆኗል።
በዚህ የአየር ሁኔታ የተነሳ በመላው አሜሪካ የተለያዩ መርሃ ግብሮችና የአውሮፕላን ጉዞ እየተሰረዙ ነው።
በሰሜን አሜሪካ ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች እጅግ ዝቅተኛ ጥራት ያለውን አየር እየማጉ ይገኛሉ።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ክስተቱን “የአየር ንብረት ለውጥ እያመጣ ያለውን ተጽህኖ የሚያመላከት ትልቅ ማናቂያ ነው” ሲሉ ገልጸውታል።
ከአሜሪካ የአየር ንብረት ጥበቃ ኤጀንሲ የወጣ የአየር ጥራት አመለካች በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ ከተሞች ትላንት ሀሙስ በዓለም ላይ ካሉ ከተሞች ሁሉ እጅግ ዝቅተኛ ጥራት ያለው አየር እንደነበራቸው ጠቁሟል።
ዋሽንግተን ዲሲ፣ ፊላዴልፊያ እና ኒው ዮርክ ሁኔታው ከከፋባቸው ከተሞች መካከል ይገኙበታል።
በካናዳው ሰደድ እሳት ሳቢያ ከተሞችን የሸፈነው ጭስ የትምህርትና ስፓርታዊ ክንውኖች እንዲሰረዙ ምክንያት ሆኗል።
በተጨሪም የተዘጉ መካነ እንስሳት ማዕከላት ያሉ ሲሆን በውስጣቸው ያሉ እንስሳትም ጭሱን ሽሽት ወደ ቤት ውስጥ እንዲገቡ ተደርጓል።
በአንዳንድ አካቢዎች ነዋሪዎች የዕለተ ተዕለት ኑሯቸውን ለመግፋት የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ለማድርግ ተገደዋል።
የአሜሪካ ከተሞችን እያጥለቀለቀ የሚገኘው ጭስ መነሻው በካናዳዋ ኪዩቤክ የተነሳው ሰደድ እሳት ሲሆን ግዛቷ ታይቶ የማይታወቅ ሰደድ እሳት እያስተናገደች ነው።
የተወሰኑ የካናዳ አከባቢዎች እጅግ የከፋ የአየር ብክለትን እየታየባቸው ነው።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር ትላንት በስለክ እንደተነጋገሩ የገለጹ ሲሆን በካናዳ የተቀሰቀሰውን ሰደድ እሳት ለመቆጣጠር አሜሪካ ከ600 በላይ የእሳት አጥፊ ባለሙያዎችን እንደምትልክ ጠቅሰዋል።
በቶሮንቶ የሚታየው ጭስ እየጨመረ እንደሚመጣና ሁኔታዎች እንደሚከፋ የገለጸው የካናዳ የአየር ንብረት መስሪያ ቤት ከቤት ውጪ የሚሆን ማንኛውም ሰው ማስክ እንዲያደርግ መክሯል።
በጭሱ ምክንያት የኒው ዮርክ ሰማይ ብርቱካናማ ቀለም ባለው ጭጋግ የተሸፈነ ሲሆን የከተማዋ መለያ የሆነችው ‘የነጻነት ሃውልት’ ጨምሮ የኒዎርክን መገለጫዎች ለእይታ አስቸጋሪ ሆነዋል።
ጭሱ ፈጣንና ዘላቂ የጤና ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል የገለጹት የህብረተሰብ ጤና ባለሙያዎች ሰዎች ወደ ውጪ እንዳይወጡ አሳስበዋል። እየታየ ካለው የሰደድ እሳት የሚወጣው ጭስ ለተዛባ የልብ ምት፣ ለደረት ህመም ሊዳርግ የሚችል ሲሆን ዓይን፣ አፍንጫና ጎሮሮ ላይም ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ይገለጻል።