ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እንግሊዝ የመንገድ ላይ ትንኮሳን በእስር ልትቀጣ ነው
እንግሊዝ በጎዳና ላይየሚፈፀሙ ፆታዊ ትንኮሳዎችን እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስራት እንደምትቀጣ አስታወቀች።
አንድን ሰው መላከፍ፣ በመንገድ ላይ መከተል እና መንገድ መዝጋትን እና መሰል ድርጊቶችን በወንጀል ለመቅጣት የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር እየሰራ መሆኑም ታውቐል።
"ሁሉም ሴት በመንገድ ለመራመድ ደህንነት ሊሰማት ይገባል" ሲሉ ሕጉን የሚደግፉት የፓርላማ አባሏ ሴኤላ ብሬቨርሜን ተናግረዋል።
ምንም እንኳን በእንግሊዝ ወሲባዊ ትንኮሳ ቀድሞውንም ወንጀል ቢሆንም የመንገድ ላይ ትንኮሳን ራሱን የቻለ ወንጀል በማድረግ ተጠቂዎች ጥቃቱ ሲፈጸም ለፖሊስ እንዲያመለክቱ ያበረታታል ተብሎ ይጠበቃል።
"የተጠቂዎችን ፍላጎት የውሳኔያችን እምብርት አድርገን እንየሰራን እንገኛለን። ይህም ማለት እነዚህን ድርጊቶች የሚፈጽሙ ወንጀለኞች የሚገባቸውን ውጤት ይቀበላሉ" ሲሉ የፓርላማ አባሏ ተናግረዋል።
ከወራት በፊት ዩጎቭ የተሰኘው ተቐም ለቢቢሲ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት ሴቶች በምሽት ብቻቸውን ሲራመዱ ደህንነት አይሰማንም ሲሉ ተናግረዋል።
ከ34 ዓመት በታች የሆኑ ሴቶች የወሲብ ጥቃት ወንጀሎች ዒላማ የመሆን እድላቸው ከፍተኛ እንደሆነ፤ ነገር ግን ወደ ፖሊስ በመሄድ የማመልከት ዕድላቸው አነስተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመልክቷል።
ባለፈው አመት በደቡብ ለንደን ወደ ቤቷ በመሄድ ላይ ሳለች በአንድ የፖሊስ አባል ታፍና ተወስዳ ተገድላ የተገኘችው የሳራ ኤቨርድ ጉዳይ በአንግሊዝ የሴቶች ደህንነትን ማስጠበቅን ጥያቄ ውስጥ ከቷል።
ከስድስት ወራት በኋላ የ28 ዓመቷ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር ሳቢና ኔሳ በደቡብ ለንደን ውስጥ በአንድ በማታውቀው ሰው ተገድላ መገኘቷ ይታወሳል።