ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዘር ማጥፋት የተጠረጠረው ትውልደ ሩዋንዳዊ በአሜሪካ ኦሃዮ በቁጥጥር ሥር ዋለ
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1994 ላይ በሩዋንዳ በተፈፀመው የዘር ማጥፋት ወንጀል ተሳትፏል የተባለ የሩዋንዳ ተወላጅ በአሜሪካዋ ኦሃዮ ግዛት በቁጥጥር ሥር ዋለ።
የፌደራል ዐቃቤ ሕግ፣ ኤሪክ ታባሮ ሺሚዬ የተባለውን ግለሰብ ሰዎች እንዲገደሉ ማድረግን ጨምሮ በጅምላ ግድያ የነበረውን ተሳትፎ በመደበቅ ከሶታል።
ሺሚዬ በአሜሪካ በሐሰት ስደተኛ ሆኖ እንዲቆይ ፈቃድ በማግኘቱ ከአውሮፓውያኑ 1995 ጀምሮ በኦሃዮ ኑሮውን ማድረጉን ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ግለሰቡ ቀደም ብሎም በዘር ማጥፋት መሳተፉን አስተባብሏል።
ቦስተን በሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
የአገር ውስጥ የወንጀል ምርመራ ልዩ ወኪል ማይክል ክሮል በመግለጫቸው እንዳሉት ሺሚዬ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ አሳዛኝ ክስተት ከሆኑት መካከል አንዱ በሆነው የዘር ጭፍጨፋ ያለውን ተሳትፎ ለመሸፈን በመዋሸቱ ነው የተከሰሰው።
ሺሚዬ በ2019 የዘር ጭፍጨፋ በመፈፀም ጥፋተኛ በተባለው ጂን ሊዮናርድ ቴጋንያ የፍርድ ሒደት ላይ ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የፍርድ ቤቱ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ ሺሚዬ ቱትሲዎች ምስማር ባለው እንጨት ጭንቅላታቸውን በመምታትና በስለት በመግደል በግሉ ተሳትፏል።
ሺሚዬ ሩዋንዳን ለቆ የወጣው በ1994 አጋማሽ ላይ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት ወደ አሜሪካ ለመግባት የአገሪቷን የኢምግሬሽን ባለሥልጣናት ዋሽቷል ተብሎ ወደተከሰሰበት ኬንያ ተጉዟል።
በዚህም በማጭበርበር፣ መረጃዎችን በመደበቅ እና በመሸፋፈን፣ ፍትሕን በማደናቀፍ እና በዳኞች ፊት በሐሰት ምስክርነት በመስጠት ክስ ቀርቦበታል።
የሺሚዬ ተከላካይ ጠበቃ ዴቪድ ጆንሰን በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ለመጠየቅ ቢቢሲ ስልክ ቢደውልላቸውም ምላሽ አልሰጡም።
እንደ አውሮፓውያኑ 1994 በሩዋንዳ በተፈፀመው የዘር ጭፍጨፋ በ100 ቀናት ውስጥ በሁቲ ጽንፈኞች በተፈፀመው ግድያ ወደ 800 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል።
የዘር ጭፍጨፋው በቁጥር አነስተኛ የሆኑትን የቱትሲ ማኅበረሰቦችን እንዲሁም የፖለቲካ ተቃዋሚዎችን እና በአጋጣሚ የተገኙ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ነበር።