የሩሲያ ጥቃት መጠናከሩን ተከትሎ ሰላማዊ ሰዎች ከዩክሬኗ ኼርሶን እየሸሹ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ13 ዓመቷ ኒካ ሴሊቫኖቫ በኼርሶን ባቡር ጣቢያ የነበረችውን ጓደኛዋ ኢናን በሁለት እጆቿ የልብ ቅርጽ ከሠራች በኋላ እጇን እያወዛወዘች ተሰናበተቻት።
ከደቂቃ በፊት እንባ ዓኖቻቸውን እስኪሞላ ተቃቅፈው ተሰነባብተዋል።
ጓደኛሞቹ መቼ በድጋሚ እንደሚገናኙ አያውቁም።
የኒካ ቤተሰብ መዳረሻቸውን ባያውቁትም ኼርሶን እየለቀቁ ነበር። ለጊዜው እርዳታ እንደሚያገኙ ተስፋ በማድረግ ወደ ምዕራባዊቷ ኽሜልኒትስኪ እያመሩ ነው።
ባለፉት ጥቂት ቀናት ለኒካ እናት ኤሌና ኼርሶን ከአቅሟ በላይ ሆናለች።
"በፊት (የሩሲያ ኃይሎች) በቀን ከሰባት እስከ 10 ጊዜ ይደበድቡን ነበር። አሁን ቀኑን ሙሉ 70 እና 80 ጊዜ ሆኗል። በጣም አስፈሪ ነው። ዩክሬንን እና ውዷን ከተማዬን እወዳለሁ። ግን መሄድ አለብን" ብላለች ኤሌና።
የሩሲያ ወታደሮች በከተማይቱ ላይ እየደረሱ ያሉት የቦምብ ድብደባ በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ከፈረንጆቹ ገና ጀምሮ ከኼርሶን ከወጡ ከአራት መቶ በላይ ሰዎች መካከል ኤሌና እና ሦስት ሴት ልጆቿ ይገኙባቸዋል።
ኤሌና በዩክሬን መንግሥት ባመቻቸው ባቡር ወጥታለች።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ብግላቸው እየወጡ ነው። ከኼርሶን መውጫ የፍተሻ ጣቢያ ላይ በፍርሃት በተሸበሩ ሰላማዊ ሰዎች የመኪና ወረፋ እየጨመረ ነው።
አይሪና አንቶኔንኮ ልናናግራት ወደ መኪናዋ ስንቀርብ እያለቀሰች ነበር።
'ከዚህ በላይ ልንሸከመው አንችልም። ድብደባው በጣም ኃይለኛ ነው። ይህንን ሁሉ ጊዜ የቆየነው ዕደለኛ ሆነን ይህም ቀን ያልፋል ብለን አሰብን ነው። ነገር ግን የጎረቤታችን ቤት ተመታ፣ የአባቴ ቤትም ተመቷል” ትላለች።

ቤተሰቦቿ ወዳሉባት በማዕከላዊ ዩክሬን ወደምትገኘው ወደ ክሪቪ ሪህ ከተማ ለመጓዝ አቅዳለች።
ባለፈው ወር በኼርሶን አስደሳች ትዕይንቶች ነበሩ። ወረራው በተጀመረ በሁለተኛው ቀን በሩሲያ ኃይሎች ስር ወድቃ የነበረችው ከተማዋ ከሳምንታት በፊት ነጻ ወጥታ ነበር።
ከሩሲያ ነፃ መውጣታቸውን ለማክበር የዩክሬይን ባንዲራ እያውለበለቡ በተሰበሰቡበት አካባቢ፤ የገና ዋዜማ ዕለት በተፈፀመ የሞርታር ጥቃት አስራ አንድ ሰዎች ሲሞቱ በደርዘን የሚቆጠሩ ቆስለዋል።
ከሟቾቹ መካከል የእርዳታ ሠራተኛ፣ የስጋ ቤት ሠራተኛ እና አንዲት በከተማው መሃል የሞባይል ሲም ካርዶችን የምትሸጥ ሴት ይገኙበታል።
የዩክሬን መንግሥት እንደገለጸው በዚያ ቀን ብቻ ኼርሶን 41 ጊዜ በሞርታር ተመትታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩሲያውያን ከዲኒፕሮ ወንዝ ግራ ሆነው እየተኮሱ ነው። የውሃው መንገድ በደቡባዊ ዩክሬን የጦር ግንባር ሆኗል።
ኼርሶን ስትራቴጂክያዊ ጠቀሜታ ያላት ክልል ስትሆን የክሬሚያ የመግቢያ በር ትባላለች። ብዙ ተንታኞች እንደሚናገሩት ሩሲያ እዚህ ቦታ የመከላከያ መስመር ለመገንባት ተገድዳለች።
ከኼርሶን ጥቃት ምን ለማግኘት እንደምትጠብቅ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው። ከሞርታር በተጨማሪ ተቀጣጣይ መሳሪያዎች ጥቅም ላይ ሲውሉ አይተናል።
የየዩክሬን ጦር በወንዙ ግራ ዳርቻ ላይ ያሉትን ቦታዎች መልሶ ለመቆጣጠር ስለመሞከሩም ግልጽ አይደለም።
በከተማዋ ከሞርታር ጥቃቶች እረፍት የምታገኝበት ጊዜ በጣም ጥቂት ነው።
የ56 ዓመቱ ሰርሂ ብሬሹን ቤቱ ተመትቶ ላዩ ላይ በመፍረሱ ተኝቶ እያለ ተገድሏል።

ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ፍርስራሹ ውስጥ ፓስፖርቱን ልትፈልግ የመጣችውን የ82 ዓመት እናቱ ታማራን አግኝተናታል። ዶክመንቶቹን የፈለገችው አስከሬኑን ከሆስፒታል ለመውሰድ ነው።
“የዛን ቀን አንድ መጠፎ ነገር እንደተከሰተ ታውቆኛል። ምክንያቱም ስልክ ደውዬለት ቤቱን እንዲለቅ ነግሬው ነበር። ባለመልቀቁ ግን ይህ ሁሉ ተፈጠረ። ሕይወታችን ተመሰቀቅሏል” ብላለች።
ከእሷ ጋር ቃለ መጠይቁን አድርገን ከመጨረሳችን ከባድ ፍንዳታዎች ተከታትለው ተሰሙ።
ኼርሶን በሙሉ አስጊ በመሆኗ ልጇ በክብር እንዲቀበር ብቻዋን ምትለፋዋ እናት አደገኛ ሥራ ላይ ናት።
በከተማዋ ቤት ውስጥም ሆነ ውጭ ሆነው መትረፍ የዕድል ጉዳይ ነው።

የ39 ዓመቷ የቀይ መስቀል ባልደረባ ቪክቶሪያ ያርሺኮ ሕይወቷ ያለፈው ከድርጅቱ የአደጋ ጊዜ መደበቂያ ጥቂት ራቅ ብላ ነው።
ቪክቶሪያ ያገኘችውን የክብር ሜዳሊያ እናቷ ሊድምይላ ቤርዛና አሳይታናለች።
“ብዙ ሰዎችን ስለረዳች ደስተኛ ነኝ። በጣም ደግ ነበረች። ሆኖም ለእኔ ህመም ነው። አገግሜ ሁለት ልጆቿን ማሳደግ ይጠበቅብኛል። እናታቸው ጀግና በመሆኗ ሊኮሩባት እንደሚገባ እነግራታለሁ” ብላለች።
ቪክቶሪያ ከሁለት ልጆቿ ጋር በመሬት ውስጥ የአደጋ ጊዜ መደበቂያ ውስጥ ትኖር ነበር። ድጋፍ ከሚሰጡት ሰዎች ጋር ቤተሰብ በመሆን ልጆቿ አሁን ኑሯቸው እዚያው ይቀጥላሉ።

“የቅርብ ሰው ሲሞት ከባድ ነው። ተስፋ ቆርጠን ከተውነው ግን ልፋቷ ከንቱ ይቀራል። ሰዎች እንዲኖሩ እንሠራለን። ሌላው ሌላው ሁለተኛ ጉዳይ ነው” ሲል ቪክቶሪያ ጓደኛ እና በጎ ፈቃደኛው ድሚትሮ ራክቲስኪ ተናግሯል።
ቤተሰቦችህ ጭምር አደጋ ውስጥ መሆናቸውን እያወቅክ መሥራት ግን ከባድ ነው።
ቦምብ በፈነዳ ቁጥር ዲሚትሮ ላይ ታች እያለ ሚስቱ ዘንድ ይደውላል። ሁለት ልጆች አሉት።
“ከዚህ መልቀቅ አይፈልጉም። ስለ እኔ ያስባሉ። ስለ እነሱ አስባለሁ። እንዲህ ነው የምንኖረው” ይላል።
“ሁሌም የሚያበሳጨኝ እነሱ [የሩሲያ ኃይሎች] የሚደበድቡት መሠረተ ልማት ነው። ቤቶች፣ መኖሪያ ህንጻዎች፣ ማሞቂያ ክፍሎች። ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያለውን አመክንዮ መረዳት ከባድ ነው” ብሏል።
“ውሃም ሆነ መብራት የለንም። አንዳንዴ ቢመጣም በድብደባው ምክንያት ይቋረጣል። ለሊት ደግሞ በጣም ያስፈራል። ጋዝ ስላለን ሙቀት እናገኛለን” ስትል ላርይሳ ሬቭቶቫ የተባለች ነዋሪ ተናግራለች።
አሁን በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኼርሶን ይኖራሉ። በዚህ ሳምንት ብቻ ግን የአካባቢው አስተዳደር ለቀው እንዲወጡ ሁለት ጊዜ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ኼርሶን በማያባራ እና ዒላማ ባለየ ጥቃት የምትታመስ ከተማ ሆናለች።












