በዩቲዩብ ስለ ልጆች አስተዳደግ የምታስተምረው አሜሪካዊት ልጆቿን በመበዝበዝ ተከሰሰች

ሩቢ የልጅ አስተዳደግ ትምህርት ስትሰጥ

የፎቶው ባለመብት, CONNEXIONS YOUTUBE CHANNEL

ታትሟል

በአሜሪካ፣ ዩታ በዩቲዩብ ላይ ስለ ልጆች አስተዳደግ በማስተማር የምትታወቀው ሩቢ ፍራንክ የተባለች አሜሪካዊት በሕጻናት ብዝበዛ ተከሰሰች።

በምግብ ማጣት ሰውነቱ የመነመነ ልጇ ከቤት ወጥቶ ከጠፋ በኋላ ነው በቁጥጥር ሥር የዋለችው።

ሩቢ ፍራንክ ከንግድ አጋሯ ጆዲ ናን ሂልድበርት ጋር ነው የታሰረችው።

ፖሊሶች የሩቢን ቤት ሲበረብሩ የ10 ዓመት ሴት ልጇም በምግብ እጦት ከስታ ተገኝታለች።

ሁለቱም ተጠርጣሪዎች ስድስት የሕጻናት ብዝበዛ ክሶች ቀርበውባቸዋል።

የ12 ዓመት ልጇ በመስኮት ዘሎ በማምለጥ ጎረቤቶችን ምግብ ሲለምን እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

“ለፖሊስ የደወሉት ጎረቤቶች ልጁን ሲያገኙት በምግብ እጦት ከስቶ፣ ሰውነቱ ላይ ቁስል ወጥቶ፣ የፕላስቲክ ገመድ ምልክት ሰውነቱ ላይ እየታየ ነበር” ሲል ፖሊስ መግለጫ አውጥቷል።

የልጁ ቁስልና የምግብ እጥረት ከፍተኛ እንደነበር ፖሊስ ገልጿል።

“በገመድ ታስሮ ስለቆየና ምግብና ውሃ ስላላገኘ ወዲያው ወደ ሆስፒታል ተወስዷል” ተብሏል።

የ10 ዓመት ልጇም ወደ ሆስፒታል ተወስዳለች።

በሩቢ ፍራንክ ቤት ፍተሻ ከተካሄደ በኋላ በአጠቃላይ አራት ልጆች በፖሊስ ተገኝተዋል።

ሁለቱ ልጆች ላይ የደረሰውን ብዝበዛ በተመለከተ ፍርድ ቤት ክስ የተመሠረተው በአካላዊ ብዝበዛ፣ በከፋ ሥነ ልቦናዊ ብዝበዛ እና በምግብ እጦት ነው።

እያንዳንዱ ክስ እስከ 10 ዓመት እስራትና 10,000 ዶላር ቅጣት ያስከትላል።

ከልጆቿ መካከል ትልቋ ሻሪ ፍራንክ እናቷ መታሰሯን ስትሰማ “በስተመጨረሻም ፍትሕ በመስፈኑ ደስተኛ ነኝ” ብላ በኢንስታግራም ገጿ ጽፋለች።

“ለዓመታት ለፖሊስ ስለ ጉዳዩ ስንወተውት ነበር። አሁን ሰሚ አግኝተናል” ስትልም አክላለች።

ከ2015 ጀምሮ በዩቲዩብ ላይ ‘8 ፓሴንጀርስ’ የተባለ ዝነኛ መሰናዶ ጀምራለች። እንዴት ስድስት ልጆቿን እንደምታሳድግ የሚገልጽ ዝነኛ መሰናዶም ነበር።

የዩቲዩብ ገጹ በዓመቱ መባቻ እስከሚዘጋ ድረስ 2 ሚሊዮን ተከታዮች ነበሩት።

ከዚህ ቀደም ልጇን ለመቅጣት ብላ ፕላስቲክ ውስጥ ለወራት ማስተኛቷንና ምግብ በመከልከልም ቅጣት እንደምትፈጽም ገልጻ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟት ነበር።

ተመልካቾች ለፖሊስ ጥቆማ ሰጥተው የነበረ ሲሆን፣ እሷ ግን “ከዐውድ ውጭ ተወስዶ ነው” ስትል ተከላክላለች።

በተጨማሪም ‘ኮኬንሽንስ’ በተባለ የዩቲዩብ ገጽ ላይ ከምትገኝ የአኗኗር አስተማሪ ጋር ቀርባለች።

ሁለቱ ሴቶች ለምን ልጆች ድባቴ ውስጥ እንደሚገቡ ሲወያዩ ተደምጧል።

“የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ልጄ ጭንቀት አለብኝ ሲል መስማት የሆነ ችግር እንዳለ ይጠቁማል” ብላ ልጆች የሰከነ ሕይወት እንዲኖራቸው እንዴት ማድረግ እንደሚቻል ትገልጻለች።

የንግድ አጋሯ የሆነችው ጆዲ ናን ሂልድበርት የወሲብ ሱስ ላለባቸው ሰዎች የሥነ ልቦና ሕክምና ትሰጥ የነበረ ቢሆንም፣ ከምታክማቸው ሰዎች የአንዱን የግል ምሥጢር ያለ ፈቃዱ በአደባባይ በማውራቷ የሥራ ፈቃዷ ለ18 ወራት ታግዷል።