አሜሪካ፡መምህሩን በጥይት ያቆሰለው የስድስት አመቱ ህጻን እናት ተከሰሰች

 ሪችኔክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

በአሜሪካ ቨርጂኒያ በሚገኝ ትምህርት ቤት መምህሩ ላይ ጥይት ተኩሶ ያቆሰለው የስድስት ዓመት ህጻን እናት ተከሰሰች።

የ25 አመቷ ዴጃ ቴይለር በልጅ ቸልተኝነት እንዲሁም በወንጀል ክስ ቀርቦባታል።

ህጻኑ አስተማሪው ላይ የተኮሰሰበት ሽጉጥ የእናቱ ዴጃ እንደሆነ ፖሊስ ቀደም ሲል አስታውቋል።

ህጻኑ በቦርሳው ውስጥ ሽጉጡን ይዞ በኒውፖርት ኒውስ ከተማ ወደሚገኘው ሪችኔክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያቀናው በጥር ወር ላይ ነበር።

ከዚያም በትምህርት ላይ እያሉ ሽጉጡን ከቦርሳው በማውጣት በመምህሩ አቢጌል ዝወርነር ላይ ተኩሷል። እጇና ደረቷ ላይ የተመታችው መምህርት ብትቆስልም በህይወት ተርፋለች።

ሰኞ እለት አቃብያነ ህግ በሰጡት መግለጫ የህጻኑ እናት በልጅ ቸልተኝነት እንዲሁም የተቀባባለ መሳሪያን በግዴለሽነት በመተውና ህጻኑን ለአደጋ በማጋለጥም ክስ ቀርቦባታል ብለዋል።

እናቲቱ ልትከሰስ የበቃችው ከጥልቅ ምርመራ በኋላ እንደሆነም አክለዋል።

የህጻኑ ቤተሰቦች ከዚህ ቀደም ከተኩሱ በኋላ በሰጡት መግለጫ ሽጉጡን ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

የቤተሰቡ ጠበቃ ጄምስ ኤልሰን ሽጉጡ በእናቱ ቁምሳጥን ውስጥ ቁልፍ ባለው መደርደሪያ ተቀምጦ እንደነበር ለአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ባለስልጣናቱ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ጥቃቱ ሊፈጸም የቻለበትን የጸጥታ ክፍተቶችን በተመለከተ ምርመራው እንደሚቀጥል የገለጹ ሲሆን ሌሎች ክሶችም ሊጨመሩ እንደሚችሉ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል።

ህጻኑ መምህሩን ተኩሶ ባቆሰለበት ዕለት ሽጉጥ ይዞ መምጣቱን ትምህርት ቤቱ ያውቅ ነበር ስትል መምህሯ የትምህርት ቤቱን ኃላፊዎች በከፍተኛ ቸልተኝነት ከሳቸዋለች።

የትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች ቀደም ሲል ህጻኑ ሽጉጥ ይዟል በሚል ጥቆማ ከደረሳቸው በኋላ በአንድ ሰራተኛ መፈተሹን አረጋግጠዋል።

አቃቤ ህግ ህጻኑ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ክስ ሊመሰረትበት እንደማይችል ተናግሯል።

አንድ ወላጅ ለዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ እንደተናገሩት ጥይቱ የተተኮሰው መምህርቷ ከታዳጊው የያዘውን ሽጉጥ ለመንጠቅ በሞከረችበት ጊዜ ነው።