ትራምፕ ስለተከሰሱባቸው ምስጢራዊ ሰነዶች ሲናገሩ የሚሰሙበት የድምጽ ቅጂ ይፋ ሆነ

ታትሟል

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ምስጢራዊ ሰነዶችን መውሰዳቸውን ሲናገሩ የሚሰሙበት የድምጽ ቅጂ በአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እጅ መግባቱ ተነገረ።

በድምጽ ቅጂው ላይ ትራምፕ የወረቀት ገጾችን ሲገልጡ እና “ይህ በጣም ምስጢራዊ ነው” ሲሉ ይሰማሉ።

የፌደራል መንግሥቱን ምስጢራዊ ሰነዶችን በአግባቡ አልያዙም በሚል የቀረበባቸውን ክስ ትራምፕ ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ ለፍርድ ቤት መናገራቸው ይታወቃል።

ሁለት ደቂቃ ያህል የሚረዝመውን የድምጽ ቅጂ ይፋ በማድረግ ሲኤንኤን የመጀመሪያው ሲሆን፣ የተቀዳውም ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞው የካቢኔ ኃላፊ ማርክ ሜዶውስ ግለ ታሪክን ለሚጽፉ ሰዎች ቃለ ምልልስ በሰጡበት ጊዜ መሆኑ ተገልጿል።

ትራምፕ “በጣም ምስጢራዊ ነው” ያሉትን ሰነድ በተመለከተም “ወረቀቶቹ እነዚህ ናቸው” በማለት ሲያብራሩ ድምጻቸው ተሰምቷል።

ነገር ግን ይህ የድምጽ ቅጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ስለመሆኑ ቢቢሲ በራሱ ያረጋገጠው ነገር የለም።

ይህ የድምጽ ቅጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ ለቀረበው ክስ ማስረጃነት በፌደራል መንግሥቱ ዐቃቤ ሕግ የቀረበ እንደሆነም ተነግሯል።

ዐቃቤ ሕግ ትራምፕ ኒው ጀርሲ ውስጥ በሚገኝ የጎልፍ መጫወቻ ሥፍራቸው ምስጢራዊ ሰነዶችን አንድ ደራሲን እና ሁለት ሠራተኞችን ጨምሮ ላልተፈቀደላቸው ሰዎች አሳይተዋል በሚል ከሷቸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ትራምፕ በሕገወጥ መንገድ ምስጢራዊ ሰነዶችን በመያዝ እና መንግሥት መልሶ እንዳይወስዳቸው በማደናቀፍ 37 ክሶች ቀርበውባቸዋል።

ነገር ግን ትራምፕ ምንም ጥፋት እንዳልሰሩ እና ከዋይት ሐውስ የወሰዷቸው ሰነዶች ምስጢራዊነታቸው ያበቁ መሆናቸውን በመግለጽ ክሶቹን አስተባብለዋል።

በሲኤንኤን እና በዋሽንግተን ፖስት ይፋ በተደረገው የድምጽ ቅጂ ላይ ትራምፕ ኢራን ላይ ጥቃት መፈጸምን ስለሚያመለክት ሰነድ ማብራሪያ ሲሰጡ ይሰማል።

በድምጽ ቅጂው መጀመሪያ አካባቢ “ኢራንን ለማጥቃት እፈልግ ነበር ይላል። ይህ አስደናቂ አይደለም?” ሲሉ ትራምፕ ይሰማሉ።

“ትልቅ የሰነዶች ክምር አለኝ፣ ይህ እንዲሁ ያነሳሁት ነው። ተመልከቱ” ይላሉ ትራምፕ በድምጽ ቅጂው ላይ።

በተጨማሪም “እንደ ፕሬዝዳንትነቴ ሰነዶቹን ከምስጢራዊዎቹ ዝርዝር ውስጥ ማውጣት እችል ነበር” በማለት “አሁን ግን አልችልም፣ ቢሆንም ግን ይህ አሁንም ምስጢር ነው።”

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ለፎክስ ኒውስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ፣ ምስጢራዊ ሰነዶችን ያልተፈቀደላቸው ሰዎች እንዲመለከቷቸው አልሰጠሁም ሲሉ አስተባብለዋል።

“ምንም ሰነድ አልነበረም። ስለ ኢራን እና ስለሌሎች ጉዳዮች ስለሚያወሱ እጅግ ብዙ ወረቀቶች ነው እየተወራ ያለው” ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።