ዶናልድ ትራምፕ በኢሊኖይስ ግዛት ወታደሮችን ማሰማራት እንደማይችሉ ፍርድ ቤት ወሰነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው የፌደራል ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ዶናልድ ትራምፕ በኢሊኖይስ የብሔራዊ ዘብ አባላትን ማሰማራት አይችሉም ሲል ወሰነ።
መቀመጫውን በቺካጎ ያደረገው የአሜሪካ የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎት ኃይሉ ለጊዜው በፌደራል ቁጥጥር ስር ሊቆይ እንደሚችል ወስኗል።
ውሳኔው በቺካጎ አካባቢ የብሔራዊ ዘብ አባላት መሰማራት "ወደ ሕዝባዊ አመፅ ሊያመራ ይችላል" በማለት የከለከለውን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ በከፊል አፅንቶታል።
ትራምፕ ከዚህ ቀደም የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን በዲሞክራቶች ወደሚመሩ ግዛቶች ሎስ አንጀለስ፣ ዋሽንግተን ዲሲ እና ፖርትላንድ ኦሪገን ከተሞች ልከዋል።
ትራምፕ የወታደሮቹ መሰማራት ሕገ ወጥ ስደትን እና ወንጀሎችን ለመቆጣጠር አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ ተከራክረዋል፤ ነገር ግን የአካባቢው ባለሥልጣናት በሕግ ከተሰጣቸው ኃላፊነት በላይ ነው በማለት ክስ መስርተዋል።
የአሜሪካ ጦር በዚህ ሳምንት በቺካጎ አካባቢ 300 የኢሊኖይስ እና 200 የቴክሳስ ብሔራዊ ዘብ አባላት ተሰማርተዋል ብሏል።
የቅዳሜው የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ "የብሔራዊ ዘብ አባላት በፍርድ ቤት ካልታዘዙ ወደተመደቡበት ግዛት መመለስ አያስፈልጋቸውም" ብሏል።
ሐሙስ ዕለት የዩኤስ ዲስትሪክት ፍርድ ቤት ዳኛ ኤፕሪል ፔሪ በኢሊኖይስ ውስጥ ወታደሮችን ማሰማራት የሚያግድ ጊዜያዊ የእግድ ትእዛዝ ሰጥተዋል።
የባይደን ተሿሚ የሆኑት ዳኛ "በኢሊኖይስ ግዛት ውስጥ አመጽ ስለመኖሩ ምንም ዓይነት አሳማኝ ማስረጃ አላየሁም" ብለዋል።
የኢሊኖይስ እና የቺካጎ ባለሥልጣናት የትራምፕ አስተዳደርን ፣ ይህ ወታደሮችን ማሰማራት "በኢሊኖይስ ሉዓላዊነት ላይ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት" ነው ሲሉ ክስ በመመስረት ተከራክረዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ለመያዝ እና ከአገር ለማስወጣት በግዛቲቱ ዘመቻ ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ቺካጎ ይህንን ውሳኔያቸውን በመቃወም ተከታታይ እርምጃ ወስዳለች።
ትራምፕ በመስከረም ወር 200 የብሔራዊ ዘብ ወታደሮችን ወደ ፖርትላንድ ኦሪገን ማሰማራታቸው አሁንም በፍርድ ቤት እያከራከረ ነው።
ባለፈው ሳምንት በትራምፕ የመጀመርያው የሥልጣን ዘመን የተሾሙት የኦሪገን ዲስትሪክት ዳኛ ካሪን ኢመርጉት ውሳኔውን አግደውታል።
አስተዳደሩ ወታደሮችን ለማሰማራት የሰጠው ምክንያት "ከእውነታው ጋር ያልተገናኘ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
በሰኔ ወር ትራምፕ 4,000 የብሔራዊ ዘብ እና 700 የባሕር ኃይል ወታደሮችን በከተማዋ ውስጥ በሚደረጉ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር የማዋል ዘመቻ ምክንያት የሚነሱ አመጽ የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎችንለማስቆም ወደ ሎስ አንጀለስ ልከዋል።
እነዚህ ወታደሮች አብዛኞቹ ለቅቀው የወጡ ቢሆንም ትራምፕ በካሊፎርኒያ ግዛት የፌደራል የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራቸታቸው ክስ መስርቷል።















