ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
መሬትን ከ 7000 ጊዜ በላይ የዞሩት ሩሲያዊ ጠፈርተኛ ህይወታቸው አለፈ
በሕዋ ላይ ለረጅም ግዜ በመቆየት ክብረወሰኑን ይዘው የቆዩት ሩሲያዊው ጠፈርተኛ በ80 አመታቸውከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
ጠፈርተኛው ቫለሪ ፖሊያኮቭ እ.ኤ.አ. በ1994 እና 1995 መካከል ሚር ተብሎ በሚጠራው የጠፈር ጣቢያ ላይ 437 ቀናትን በፈጀ ቆይታ ምድርን በመዞር ነው ክብረ ወሰኑን ይዘው የቆዩት።
እንዲሁም ወደ ማርስ ረጅም ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች የአዕምሮ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይችሉ እንደሆነ ለማረጋገጥ በተሰሩ ጥናቶች ላይ ተሳትፈዋል።
ለ 14 ወራት በሕዋ ላይ በመቆየታቸው ምክንያት የአዕምሮአቸው ተግባራት (ኮግኒቲቭ ፋንክሽን) ላይ ምንም አይነት እክል አለመኖሩ በጥናቱ ተረጋግጧል።
የፖሊያኮቭ ህልፈት የተገለፀው በሩሲያ የጠፈር ኤጀንሲ ሲሆን ኤጀንሲው የሶቪየት ኅብረት ጀግና ብሎም የዩኤስኤስአር አብራሪ ጠፈርተኛ የሚሉትን ማዕረጋቸውን ተጠቅሟል።
እስካሁን ድረስ የፖሊኮቭ ህልፈት መንስኤ በይፋ አልተገለጸም።
ኤጀንሲው አክሎም የፖሊኮቭ ጥናት የሰው ልጅ አካል ከምድር ምህዋር አልፎ ጥልቅ የጠፈር በረራዎችን ማስተናገድ እንደሚችል ለማረጋገጥ ረድቷል ሲል ግለጿል።
ጠፈርተኛው ፖሊያኮቭ በ1942 ከሞስኮ በስተደቡብ በምትገኘው ቱላ ተብላ በምትጠራው ከተማ ነበር የተወለዱት።
ለመጀመሪያ ግዜ ወደ ጠፈር የተጓዙት እኤአ በ1988 ሲሆን ጉዟቸውም ስምንት ወራትንያስቆጠረ ነበር።
ፖሊያኮቭ በዘጠናዎቹ አጋማሽ ላይ በሚር የጠፈር ጣቢያ ላይ በቆዩበት ወቅት መሬትን ከ 7,000 ጊዜ በላይ እንደዞሩ ተዘግቧል።
በኋላ ላይ የጉዟቸው ቆይታ ወደ ማርስ ደርሶ የመመለስ ያህል እንደሆነ ተናግረውም ነበር።
ጠፈርተኞች ወደ ምድር ሲመለሱ ከስበት ጋር ተለማምደው ለመራመድ ስለሚቸገሩ በሰዎች እርዳታ ከመንኩራኩራቸው እንዲወርዱ ይደረጋል። ፖሊያኮቭ ግን ከጠፈር ሲመለሱ ከመንኩራኩሩ ሰዎች ተሸክመዋቸው እንዲወጡ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።
ሚር የጠፈር ጣቢያ እኤአ በ1986 መጀመሪያ ላይ በቀድሞው ሶቭየት ህብረት በኋላ ላይም በሩሲያ ቁጥጥር ስር ሆኖ ወደ ምህዋር ተላከ።
በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የተሰማራችው 135 ሺህ ኪ.ግ. የምትመዝነው ሳተላይት ሶቭየት ሕብረት እና በአሜሪካ ለረጅም ጊዜ የቆየ የፖለቲካ ውጥረት ውስጥ ቢሆኑም በጋራ ይገለገሉባት ነበር።