በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አማጺያን በጠሩት ሰልፍ ላይ በደረሰ ፍንዳታ በርካታ ሰዎች ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በምትገኘው እና በቅርቡ በአማጺያን ስር በወደቀችው ከተማ በተጠራ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተኩስ እሩምታ እና ፍንዳታ ተከሰተ።

በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ሁለተኛዋ ትልቋ ከተማ በሆነችው ቡካቩ የተፈጠረውን ፍንዳታ ተከትሎ ህዝቡ በድንጋጤ ከሰልፉን ስፍራ ሲሸሽ እና በጎዳናዎች ላይ አስከሬኖች እንደነበሩ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።

የሟቾች ቁጥር ግልጽ ባይሆንም አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የሆስፒታል ምንጭን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ቢያንስ 11 ሰዎች ሲሞቱ 60 የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል።

በሩዋንዳ የሚደገፉት አማጺያን ፈጣን ግስጋሴ በማድረግ ከተማይቱን ከመንግሥት ኃይሎች ከተቆጣጠሩ በኋላ በቡካቩ ያደረጉት የመጀመሪያው ሰልፍ ነበር።

የፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ መንግሥት ጥቃቱን አቀናብሯል ሲሉ አማጺያኑ ከሰዋል።

ትሺሴኬዲ በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል እየተንቀሳቀሰ ያለው "የውጭ ጦር" ላይ ጣታቸውን ቀስረዋል።

በሩዋንዳ የሚደገፈውን ኤም23ን ጨምሮ የሌሎች የአማጺ ቡድኖች ጥምረት መሪ የሆነው ኮርኔይል ናንጋ በሰልፉ ላይ ተገኝቶ ንግግር አድርጎ ነበር።

አማጺያኑ በከተማዋ ደህንነትን እና ሠላምን እንደሚያሰፍን ለህዝቡ ቃል ገብቷል።

"በሁሉም አካባቢዎች የሚደረጉ ልዩ ጥበቃዎች ይኖራሉ" ሲል መግለጹን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ጥቃቱ በቡካቩ ዋና አደባባይ በተፈጸመበት ወቅት ናንጋ እና የኤም23ቱ በርትራንድ ቢሲምዋ ከስፍራው ቀድመው ብለው እንደወጡ ይታመናል።

ናንጋ በሰጠው መግለጫ ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች መያዛቸውን እና ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።

"በዚህ የፈሪ እና አረመኔያዊ ድርጊት የተሳተፉ የእጃቸውን ሳያገኙ አይቀሩም" ብሏል።

አማጺያኑ ከጥር ወር ጀምሮ በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ወደፊት እየገሰገሱ ሲሆን በአካባቢው ትልቅ የሆነችውን ጎማን ጨምሮ ቡካቩን ተቆጣጥረዋል።

ጦርነቱ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ በማድረግ ቀድሞውንም የከፋ የነበረውን ሰብአዊ ቀውስ እንዳባባሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና አማጺያኑ አሁን ከተቆጣጠሩት አካባቢ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ሩዋንዳ ኤም23ን እንደማትደግፍ ከዚህ ቀደም ትገልጽ የነበረ ሲሆን በቅርቡ ግን በዲሞክራቲክ ኮንጎ እና በሩዋንዳ ድንበር አካባቢ የሚደረገው ውጊያ ለደህንነቷ አስጊ መሆኑን ገልጻለች።

ከሦስት ሺህ እስከ አራት ሺህ የሚደርሱ የሩዋንዳ ወታደሮች በምስራቃዊ በዲሞክራቲክ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እንደሚንቀሳቀሱ የተባበሩት መንግስታት ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ግምታቸውን አስቀምጠዋል