የእስር ቤት ጠባቂዎችን ያገቱት የኢኳዶር ነውጠኛ እስረኞች 57 የሚሆኑትን ለቀቁ

በኢኳዶር አደገኛ ቦዘኔዎች ፖለቲከኞችን ያስገድላሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, በኢኳዶር አደገኛ ቦዘኔዎች ፖለቲከኞችን ያስገድላሉ
ታትሟል

በስድስት የኢኳዶር እስር ቤቶች የሚገኙ አደገኛ እስረኞች የእስር ቤት ጠባቂዎቻቸውን ካገቱ በኋላ 57 የሚሆኑነት መፍታታቸው ተሰማ።

ከእገታ ከለቀቋቸው 50 የእስር ቤት ጠባቂዎች ሌላ ሰባት የፖሊስ አባላትንም ፈተዋል።

እገታው የተቀነባበረው በአደገኛ ቦዘኔ የወንጀል ቡድኖች መሆኑ ተሰምቷል።

የአደገኛ ቦዘኔ ቡድኖቹ ጥቅማችን አደጋ ውስጥ ገብቷል ብለው በመቆጣታቸው ነበር ይህን እገታ ያቀነባበሩት።

የአደገኛ እጽ ቁጥጥር ቢሮ በሚገኝበት በዋና ከተማዋ ኩዊቶ የፈነዳው በመኪና የተጠመደ ቦምብ በነዚህ ቡድኖች የተቀነባበረና ይኸው ቁጣ ያስከተለው ነው ተብሏል።

ፖሊስ በግዙፍ እስር ቤቶች ውስጥ የጦር መሣሪያ ፍተሻ ማድረጉን ተከትሎ ነበር የተቆጡ የአገሪቱ አደገኛ ቦዘኔ አባላት ባስተላለፉት ትእዛዝ በመላ አገሪቱ እስረኞች የማረሚያ ቤት ጠባቂዎቻቸውን እንዲያግቱ መመሪያ ያስተላለፉት።

በእስር ቤት ነውጥ እንዳይከተል በመስጋት በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ አባላት እና ወታደሮች ከዋና ከተማዋ ኩዊቶ 88 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘውን ኮቶፓክሲ ማረሚያ ቤት ሲፈትሹ ነበር።

ነገር ግን ታግተው የቆዩት የእስር ቤት ጠባቂዎችና የፖሊስ አባላት በምን አግባብና ሁኔታ ከእገታ እንደተፈቱ የተገለጸ ነገር የለም።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዐርብ በኤክስ ሰሌዳቸው እንዳስረዱት ግን እገታው መንግሥታቸው በእስር ቤቶች ውስጥ ፍተሻ ማድረጉን ተከትሎ የተቆጡ የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን አባላት መንግሥትን ለማስፈራራትና ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ለማድረግ ያደረጉት ከንቱ ሙከራ ነው ብለዋል።

ኢኳዶር አደገኛ ዕጽ የሚያዘዋውሩ አደገኛ ቦዘኔዎች በስፋት የሚገኙባትና ‘የእጽ ጌቶች’ የመንግሥትን መዋቅር እስከማወክ የደረሱ እንደሆኑ ይነገራል።

በዚህ የተነሳ በርካታ ታሳሪዎች ስለሚገኙ በአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች የተጣበቡና በቂ አቅርቦት የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓል።

በማረሚያ ቤቶች ውስጥ በሚነሱ ነውጦች በየጊዜው በርካታ እስረⶉች ይገደላሉ።

በእስር ቤቶች የአደገኛ ቦዘኔ ቡድን አመራሮች ስለሚገኙ መንግሥት እነርሱ የማይፈቅዱትን ድርጊት ሲፈጽም ከፍተኛ ነውጥ ያስነሳሉ፣ እስረኞችን ያግታሉ ይገድላሉ።

በኢኳዶር ድጋሚ ምርጫ ለማድረግ ሁለት ወራት ብቻ ነው የሚቀሩት።

ከሳምንታት በፊት፣ ቀጣይ የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ተብሎ ተስፋ የተጣለባቸው ሰው በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መገደላቸውን ተከትሎ ሌሎች እጩዎች ለሕይወታቸው መስጋት ጀምረዋል።

ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው እጩዎች አንዷ የሆኑት ሉዊዛ ጎንዛሌዝ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከመንግሥት ጥበቃ በተጨማሪ ልዩ የጥይት መከላከያ ሰደሪያ ለመታጠቅ እንደሚገደዱ አስታውቀዋል።

ሉዊዛ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ብቻም ሳይሆን 24 ሰዓት ጥይት መከላከያውን አላወልቅም ብለዋል።