የኤምአይ 5 እና የኤፍቢአይ መሪዎች ቻይና ‘ከባድ ስጋት’ ደቅናለች ሲሉ አስጠነቀቁ

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ክሩስቶፎር ሬይ እና የኤምአይ 5 ዳይሬክተር ኬን ማካሉም

የፎቶው ባለመብት, UK POOL VIA ITN

ታትሟል

የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) እና የአሜሪካ የደኅንነት አገልግሎት ኃላፊዎች ከቻይና እየመጣ ያለውን ስጋት ለማስጠንቀቅ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሁለቱ የደኅንነት ተቋማት ኃላፊዎች በጋራ በተለይም በቻይና ጉዳይ መግለጫ ሲሰጡ ይህ የመጀመሪያቸው መሆኑ ተነግሯል። ኃላፊዎቹ ከቻይና የሚመጣው ስጋት ከፍተኛ እና ሁሉን አቀፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በእዚሁ የሁለትዮሽ መግለጫ የኤፍቢአይ ዳይሬክተሩ ክርስቶፎር ሬይ “ለምጣኔ ሃብታችን እና ለብሔራዊ ደኅንነታችን ቻይና ከፍተኛ እና የረጅም ጊዜ ስጋት እየሆነችብን ነው” ያሉ ሲሆን፣ በቅርቡ የተካሄደውን ምርጫ ጨምሮ ቻይና በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንደምትገባ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም የደኅንነት ተቋም ኤምአይ 5 ኃላፊ ኬን ማክለም እንዳሉት ደግሞ፣ እያደገ የሚመጣውን ስጋት ተከትሎ ቻይናን በተመለከተ የሚሰሩ ሙያተኞቻቸውን ቁጥር ባለፉት ሦስት ዓመታት እጥፍ አድርገዋል። ስጋቱን ግምት ውስጥ በማስገባት አሁንም በእጥፍ ለማሳደግ ማቀዳቸውን ገልጸዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የቻይናን ኮሚኒስት ፓርቲ በተመለከተ የሚሰሩ የዩኬ የደኅንነት ሙያተኞች በ2018 ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ቢያንስ በሰባት እጥፍ ጨምሯል።

የአሜሪካ ፌደራል ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኤፍቢአይ ዳይሬክተሩ ሬይ ቻይና ታይዋንን በኃይል የምትጠቀልል ከሆነ “ዓለም አይታው የማታውቀው አስከፊ የንግድ መስተጓጎል ይገጥማታል” ብለዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገው የሁለቱ የደኅንነት ተቋማት የጋራ መግለጫ ለንደን ውስጥ በኤምአይ 5 ቢሮ ነው የተሰጠው። 

በቻይናው ኮሚኒስቲ ፓርቲ ተነድፏል ያሉትን ተግዳሮት የዩኬው ደኅንነት ዳይሬክተር ማክለም “ጨዋታ ቀያሪ” ሲሉት የአሜሪካው ሬይ ደግሞ “ትልቅ” እና “ትንፋሽ መውሰጃ” ብለውታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተጨማሪም ሬይ የቴክኖሎጅ እና ቢዝነስ ሰዎችን የቻይና መንግሥት በርካታ መሣሪያዎችን በመጠቀም “ቴክኖሎጃችሁን ሊሰርቃችሁ ነው” በማለት አስጠንቅቀዋል።

“በጣም ተራቀናል የሚሉ የቢዝነስ ሰዎች ከሚያስቡት በላይ ለምዕራባውያን ምጣኔ ሃብት እጅግ አደገኛ ነው” ያሉት ሬይ፣ በገጠሪቱ የአሜሪካ ክፍል የሚሰሩ የቻይና ኩባንያዎች በተራቀቀ ቴክኖሎጂ እና በረጅም የጊዜ ሂደት የሚያጋብሱትን ቢሊዮን ዶላር በማሳያነት አንስተዋል።

ከእዚህም በተጨማሪ ቻይና የሳይበር ሙያተኞችን ያሰማራች ሲሆን ዓላማቸውም “ማጭበርበር እና በግዙፉ መዝረፍ” ሲሆን የእነዚህ ሙያተኞች ቁጥርም የሌሎች አገራት የሳይበር ሙያተኞች ተደምረው የማይደርሱበት ነው ብለዋል። 

ኤፍቢአይ በቅርቡ በተደረገው የአሜሪካ የኮንግረስ ምርጫ በተለይ ኒውዮርክ ውስጥ የቻይና መንግሥት የማይፈልገውን ተወካይ ላለማስመረጥ በቀጥታ ተሳትፏል ሲሉም ከሰዋል።   

ቻይና ታይዋንን በኃይል ከያዘች ዓለም አይታው የማይታወቅ እና ከሩሲያ እና ከዩክሬን ጦርነት የከፋ የንግድ መስተጓጎል ይገጥማታል። ቻይና ውስጥ የሚገኙ የምዕራባዊያን የንግድ ተቋማትም መያዣ ሊሆኑ እንደሚችሉ የኤፍቢአይ ዳይሬክተሩ ክርስቶፎር ሬይ ተናግረዋል። 

የዩናይትድ ኪንግደም የደኅንነት ተቋም ኃላፊ በበኩላቸው አዲሱ ሕግ ስጋቱን ለመከላከል አስተዋጽኦ ቢኖረውም ሁሉም ማኅበረሰብ ስለአደጋው ተገንዝቦ እንዲሰራ ዩኬም “ጠንካራ ዒላማ” ሊኖራት ይገባል ብለዋል።

አሁን የተደረገውን የቪዛ ሥርዓት ተከትሎ 50 ተማሪዎች ከቻይና የመከላከያ ሠራዊት ጋር ግንኙነት ያላቸው በመሆኑ ዩናይትድ ኪንግደምን ለቀዋል ብለዋል።

ከቻይና የሚመጣው ስጋት ከባድ እና ፈታኝ መሆኑን የገለጹት የአሜሪካው የደኅንነት ቢሮ ኃላፊ ቻይናን በክትትላቸው ስር ማቆየት ቀላል አይሆንም ብለዋል።