የጣልያኑ ናፖሊ ከ33 ዓመት በኋላ የሴሪ አ ዋንጫን አነሳ

ታትሟል

የጣልያኑ ክለብ ናፖሊ ከ33 ዓመታት በኋላ የአገሪቱን ሊግ ሴሪ አ ዋንጫ አንስቶ ለረጅም ጊዜ ይህንን ድል ሲጠብቁ ለነበሩ ደጋፊዎቹ ታላቅ ደስታ ፈጥሯል።

ናፖሊ ለመጨረሻው ጊዜ የሴሪ አ ዋንጫን ያነሳው በአውሮፓውያኑ 1990 የእግር ኳስ ኮከቡ ዲያጎ ማራዶና ለቡድኑ በሚጫወትበት ጊዜ ነበር።

ከዩዲኒዜ ቡድን ጋር ለፍጻሜ የተጫወተው ናፖሊ አንድ ከዜሮ ከመመራት ተነስቶ አቻ በመሆን ነጥብ ተጋርቶ ነው ዋንጫውን ማንሳት የቻለው።

በጨዋታው ናፖሊ አንድ አቻ በመውጣት ነጥብ እንዲጋራ እና የሴሪ አ ዋንጫን እንዲያነሳ ያስቻለው ናይጄሪያዊው አጥቂ ቪክተር ኦሲምሄን ነው።

ቪክተር ቡድኑ ዋንጫ ባነሳበት የውድድር ዘመን በ26 ጨዋታዎች 21 ግቦችን በማስቆጠር ዝናን አትርፏል።

ናፖሊ ለሦስተኛ ጊዜ የሴሪ አ አሸናፊ የሆነው ቀሪ ጨዋታዎች እያሉት ነው።

“የናፖሊ ደጋፊዎችን ደስታን ማየቱ ብቻ ዋንጫው ምን ያህል ሲጠበቅ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል” ሲሉ የናፖሊ ቡድን አሰልጣኝ ሉቻኖ ስፓሌቲ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ናፖሊ ከዚህ ቀደም ያነሳቸው የሴሪ አ ዋንጫዎች ማራዶና ለቡድኑ በሚጫወትባቸው ከ30 ዓመታት በፊት በተከታታይ ነበር። ለዚህም የቡድኑ ስታዲየም በስሙ እንዲጠራ ተደርጓል።

ከዚያ በኋላ ግን ክለቡ በከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ገብቶ ከሴሪ አ ለመውረድ ከባድ ኪሳራ ገጥሞት ነበር። ለዓመታትም በታችኛው የሴሪ ሲ ሊግ ውስጥ ለመጫወት ተገዶ ነበር።

በአሁኑ ጊዜ ግን ናይጄሪያዊውን ቪክተር ኦሲምሄንን እና ጆርጂያዊውን ክቫራትስኼሊያን የመሳሰሉ ኮከብ ተጫዋቾች ያሉት ናፖሊ ወደ ሴሪ አው ድል ለመመለስ ችሏል።

የቡድኑ አሰልጣኝ የ64 ዓመቱ ሉቺያኖ ስፓሌቲ ከናፖሊ ጋር የሊጉን ታላቅ ዋንጫ ሲያነሱ፣ በሴሪ አ ታሪክ በዕድሜ የገፉ አሰልጣኝ ለመሆን በቅተዋል።

ናፖሊ ከሳሌርኒታና ጋር የነበረውን ጨዋታ ማሸነፍ ችሎ ቢሆን ኖሮ ዋንጫውን ባለፈው ሳምንት ማንሳት ይችል ነበር። ነገር ግን አቻ በመለያየቱ አንድ ነጥብ ለማግኘት ከዩዲኒዜ ጋር ያደረገውን የሐሙስ ምሽት ጨዋታውን መጠበቅ ነበረበት።

አምስት ጨዋታዎች እየቀሩት የሊጉ አሸናፊ የሆነው ናፖሊ፣ በደረጃ ሰንጠረዡ ሁለተኛ ሆኖ ከሚከተለው ላዚዮ በ16 ነጥብ በልጦ ነው ዋንጫውን ያነሳው።