ቤንያሚን ኔታንያሁ ትራምፕ 'ጋዛ በአሜሪካ እጅ ትሆናለች' ማለታቸውን አደነቁ

የአሜሪካው ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፍልስጤማውያንን ከመሬታቸው ጋዛ አፈናቅሎ ወደ ሌሎች አገራት ለማስፈር የያዙት እቅድ "እውን ለማድረግ" እየሰሩ መሆኑን ተናገሩ።

ቤንያሚን ኔታንያሁ እሁድ ዕለት በኢየሩሳሌም ከአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ጋር ከተገናኙ በኋላ በፍልስጤም ግዛት "የጋራ ስትራቴጂ" ላይ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ውይይቱ የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ ጋዛን እንድትወስድ እና እዚያ የሚገኙትን ሁለት ሚሊዮን ፍልስጤማውያን ወደ ጎረቤት አገራት እንድታፈናቅል ሀሳብ ካቀረቡ በኋላ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማንኛውንም ዜጋ በቁጥጥር ስር ከሚገኘው ግዛት በግዳጅ ማፈናቀል "ከዘር ማጽዳት ጋር የሚስተካከል" እንዲሁም በዓለም አቀፍ ሕግ በጥብቅ የተከለከለ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

የአሜሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት የፕሬዚዳንት ትራምፕ እቅድ ሰዎችን "ሊያስደንቅ እና ሊያስደነግጥ ይችላል" ነገር ግን ከዚህ ቀደም ከነበሩ "እርባና ቢስ ሀሳቦች" በተሻለ ሌላ አማራጭ ሀሳብ ለማቅረብ "ድፍረት" ይጠይቃል ብለዋል።

ኔታንያሁ እርሳቸው እና ሩቢዮ የትራምፕን የማፈናቀል ራዕይ ተግባራዊ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ መወያየታቸውን ገልጸው አሜሪካ እና እስራኤል በጋዛ ላይ አንድ አቋም አላቸው ብለዋል።

የእስራኤሉ መሪ በትጥቅ ቡድኑ ሃማስ የተያዙ እስራኤላውያን ታጋቾች በሙሉ ካልተለቀቁ "የገሃነም በሮች" እንደሚከፈቱ አስጠንቅቀዋል።

ሩቢዮ ደግሞ "ሀማስ እንደ ወታደራዊ ወይም የመንግሥት ኃይል ሊቀጥል አይችልም። ገዢ ወይም አስተዳዳሪ ወይንም ኃይል እና ሁከትን በመጠቀም ማስፈራራት እስከቀጠለ ድረስ ሰላም የማይታሰብ ይሆናል" ብለዋል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው መወሰዳቸው ይታወሳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስራኤል በጋዛ ውስጥ በፈጸመችው ጥቃት ከ48, 280 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

16 ወራት በዘለቀው ጦርነት በጋዛ ከፍተኛ ውድመት ያስከተለ ሲሆን፣ አብዛኛው የጋዛ ሕዝብ በተደጋጋሚ የተፈናቀለ ሲሆን፣ ወደ 70% የሚጠጉ ሕንፃዎች ፈራርሰዋል ወይም ወድመዋል።

በጋዛ ሰርጥ የጤና፣ የውሃ፣ የአካባቢ ጽዳትና የግል ንፅህና አጠባበቅ ስርዓቶች ወድመዋል እንዲሁም የምግብ፣ የነዳጅ፣ የመድሃኒት እና የመጠለያ እጥረት ተከስቷል።

የፍልስጤም እና የአረብ መሪዎች የትራምፕን ጋዛን የመጠቅለል እቅድ የተቃወሙት ሲሆን፣ የፍልስጤም አስተዳደር እና ሃማስ በበኩላቸው የፍልስጤም መሬት "ለሽያጭ አይቀርብም" ሲሉ አቋማቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም አሜሪካ ስታደርጋቸው ከነበሩ የሰላም ጥረቶች በተለየ፣ እስካሁን ድረስ የዩኤስ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች የፍልስጤም መሪዎችን አግኝተው ስለጋዛ የወደፊት ሁኔታ አላነጋገሩም።

ኔታንያሁ እና ሩቢዮ እሁድ እለት በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የሃማስ አስተዳደር አቅምን ከግዛቱ ለማጥፋት፣ ኢራንን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ እና ከአሳድ በኋላ በሶሪያ ያለውን ሁኔታ መከታተልን የሚሉ ጉዳዮችን ላይ በዝርዝር መወየየታቸውን ጉዳዮች ጠቅሰዋል።

ሩቢዮ በመቀጠል ቴህራንን "ከእያንዳንዱ የአመፅ ድርጊት ጀርባ፣ ከእያንዳንዱ የማተራመስ እንቅስቃሴ ጀርባ፣ ሰላምና መረጋጋትን ከሚያደፈርሱ ነገሮች በስተጀርባ" አለች ሲሉ ከስሰዋል።

ኔታንያሁም ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) የወጣውን የእስር ማዘዣ "አፍራሽ ሕግ" በማለት እስራኤልን "በአስደንጋጭ ሁኔታ ፈርጇል" በማለት አውግዘዋል።

ባለፈው ዓመት ኔታንያሁ እና የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስትራቸው በጋዛ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል በሚል የእስር ማዘዣ ያወጣው ፍርድ ቤት ላይ የትራምፕ አስተዳደር ማዕቀብ በማውጣቱ አመስግነዋል።

ሩቢዮ በመካከለኛው ምስራቅ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው እስራኤልን እየጎበኙ ነው።

ዩክሬንም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ባልተጋበዙበት የሳዑዲ አረቢያው ስብሰባ በዩክሬን ጦርነት ላይ ለመነጋገር በመጪዎቹ ቀናት ከሩሲያ ባለስልጣናት ጋር ይገናኛሉ።

የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጉብኝት በአሜሪካ የተሰሩ ከባድ ቦምቦች እስራኤል ከደረሰ በኋላ የተካሄደ ነው።