የዩክሬን ወታደር ሲቀላ ያሳያል የተባለው ቪዲዮ ፕሬዚዳንት ዜለንስኪን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩክሬን ወታደር በአንድ ሩሲያዊ ሲቀላ ያሳያል የተባለው ቪዲዮ መውጣቱን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ ዓለም አቀፍ መሪዎች ምላሽ እንዲሰጡ ጠየቁ።
“ሁሉም ምላሽ ሊሰጡ ይገባሉ፤ እያንዳንዱ መሪ። ይህ እስኪረሳ ድረስ አትጠብቁ” በማለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ተናግረዋል።
የዩክሬን የደህንነት አገልግሎት “የጦር ወንጀል” ሲል የጠራውን የወታደሩን ግድያ እያጣራሁ ነው ብሏል።
ሩሲያ በምላሹ ቪዲዮው አሰቃቂ ነው ብትልም ትክክለኛነቱ እንዲሁም የፈጸመው አካል ሊጣራ ይገባል ብላለች።
ቪዲዮው በተንቀሳቃሽ ስልክ የተቀረጸ የሚመስል ሲሆን ወቅቱም በጋ ወራት ሊሆን እንደሚችል ተገልጿል። ቪዲዮው በዩክሬን ወታደሮች ክንድ ላይ የሚጠለቀውን ቢጫ አርማ የለበሰ ግለሰብንም ያሳያል።
በሌላ በኩል ወንጀሉን ፈጽሟል የተባለው ግለሰብ ደግሞ የሩሲያ ወታደሮች መለዮ የሆነውን በእግር ላይ የሚጠለቀውን ነጭ አርማ ለብሶም ይታያል።
የሩሲያ ቋንቋ በሆነው ሩስኪ ሲነጋገሩ የሚሰማ ቢሆንም ዩክሬናውያንም ቋንቋውን ስለሚናገሩ ይህ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም ተብሏል።
በዚህ አጭር ቪዲዮም ላይ ቢጫ የክንድ አርማ ያጠለቀ ግለሰብ በእግሩ ላይ ነጭ አርማ ባጠለቀ በለበሰ ትልቅ ቢላዋ አንገቱ ሲቀላም ያሳያል።
በዚህ ቪዲዮ ላይ አንደኛው ግለሰብ የዩክሬንን ግዛት ምልክት ያለበትን ባጅ አድርጎም ያሳያል።
የባጁ ቀለሞች እና ቅርጽ የዩክሬን ጦር ኃይል ከሚያደርገው ምልክት ጋር ተመሳሳይ ነው።
ሆኖም ይህ ባጅ በአንድ የኮሚክ መጽሃፍ ገጸ ባህሪ የሆነውን ‘የፐኒሸር’ የራስ ቅል ምልክትን ይመስላል። ይህንንም ምልክት በጦርነቱ በሁለቱም በኩል ባሉ ተዋጊዎችም ሲለበስም ታይቷል።
በተጨማሪም በቪዲዮው ላይ አረንጓዴ ቀለም ያለው ፓስፖርት ሰነድ መሬት ላይም ይታያል። ፓስፖርቱ በቪዲዮው ላይ ተገልብጦ የሚታይ ሲሆን ከዩክሬን ወታደራዊ መታወቂያ ቀለምም ጋር ተመሳሳይ ነው ተብሏል።












