ከማያውቁት ሰው ጋር መኖር ደስተኛ ያደርጋል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኑሮ ውድነት እና የብቸኝነት ስሜት ሰዎች ደባል እንዲፈልጉ ምክንያት ሆኗል።
የዓለም ጤና ድርጅት ብቸኝነት ዓለም አቀፍ ስጋት ነው ብሏል። የኑሮ ውድነትም የበርካቶች ራስ ምታት ሆኖ ቀጥሏል።
ብዙዎች በጋራ መኖርን እንደ አማራጭ እየወሰዱ ይገኛሉ።
ለመተኛት ሲሞክሩ ሙዚቃ ሊጮህ ወይም እቃ ሳይታጠብ ሊጠብቅዎ ይችላል። ሆኖም ግን ከሌሎች ጋር መኖር ጥሩ ስሜት ይሰጣል ብለው የሚከራከሩም አሉ።
ሮዚ ኬሌት 30 ዓመቷ ነው። ለንደን ውስጥ ስለ ምግብ ትጽፋለች። በ2020 ከፍቅረኛዋ ጋር ስትጣላ መኖሪያ መፈለግ ጀመረች።
'ሀክኒ ዊክ' የተባለ ቦታ ያገኘችው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነው። ቢያንስ 100 በማኅበር መኖሪያዎች አሉት።
አብረዋት በ20ዎቹ መጨረሻና በ30ዎቹ መጀመሪያ ያሉ ስድስት ሰዎች ይኖራሉ።
የቤት እቃ ለመግዛት፣ ለአስቤዛ እና ሌሎችም የቤት ወጭዎች ደባሎቹ 25 ፓውንድ ያዋጣሉ። ሁሉም ሰው በየተራ ያበስላል።
አንድ ሰው እንግዳ ይዞ የሚሄድ ከሆነ ቀድሞ ያሳውቃል።
የደባሎች ስብሰባ ያደርጋሉ። የተቀየመ ሰው ካለ ስሜቱን ይገልጻል።
አብሮ መኖር ያለው ጥቅም ሁሌም የሆነ ሰው ከጎኔ መኖሩ ነው ትላለች ሮዚ።
“ለንደን ቤት ውድ ነው። እዚህ ግን ጥሩ ኑሮ እንገፋለን” ስትል ትገልጻለች።
መሰናክልም አለው። “አንዳንዴ ብዙ ሰዎች ካሉት ትልቅ ጠረጴዛ ውጭ ራሴን ማግኘት እፈልጋለሁ። የሁሉም ነገር ድምጽ ይሰማል” ስትል ስለ አኗኗራቸው ታስረዳለች።
“ሁለት ሻወርና ሁለት ሸንት ቤት አለን። እቃ ማጠቢያችን ግን አንድ ብቻ ነው። አይበቃንም” በማለትም ታክላለች።
አንዳንድ የጋራ ቤቶች ውስጥ ለዓመታት መቆየት ይቻላል። ሌሎቹ ደግሞ ለውስን ጊዜ የሚዘጋጁ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሪያል ዜሪንግ 36 ዓመቷ ነው።
እሷ፣ ባለቤቷና ሦስት ልጆቻቸው በአሜሪካ የጋራ ቤት ውስጥ ይኖራሉ።
“ባለቤቴ አንደኛውን ክፍል ገዝቶት ነበር። የገዛው ገና ሳንጋባ ነበር። ከሰዎች ጋር መኖር ምን ማለት እንደሆነ ስለሚገባኝ በሐሳቡ ደስ አለኝ። እስካሁንም እየኖርን ነው” ትላለች።
'አርብኮ ኮ ሀውሲንግ ኢስቴት' ይባላል። ሁለት ሕንጻ አለው። እያንዳንዱ ክፍል መኝታ ቤት፣ ሻወር እና ኩሽና አለው።
“እንደ ኮንዶሚንየም ነው። ቤቱ የኛ ቢሆንም በየወሩ እንከፍላለን። የጋራ ቤታችን የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን ይውላል” ስትል ትገልጻለች።
በየሳምንቱ ነዋሪዎች ምግብ እያዘጋጁ ያቀርባሉ። የሙዚቃና ሌሎችም የጋራ ክንውኖችም ያዘጋጃሉ።
በየጊዜው ስብሰባ ያካሂዳሉ።
“እኔ ሙሉ ሰዓት ነው የምሠራው። ጡረታ የወጡ ግን አሉ። እነሱ አብረው ብዙ ነገር ያደርጋሉ” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
“በጣም ዋጋ የምሰጠው በመካከላችን ወላጅ የሆኑ ሰዎች መኖራቸውን ነው። አዲስ እናት ሳለሁ እነሱ ናቸው ብዙ ነገር ያስተማሩኝ” ትላለች።
ከሥራ ስትመለስ ልጆቿን ከሌሎች ልጆች ጋር ታጫውታለች።
በዩናይትድ ኪንግደም ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የጋራ ቤቶች ቁጥር መጨመሩን ጥናት ያሳያል። በሌላ በኩል የኑሮ ውድነት ያሳደረው ጫና ይጠቀሳል።
'ዲገርስ ኤንድ ድሪመርስ' የተባለ የጋራ መኖሪያ የቦር ኃላፊ የሆነችው ፔኒ ክላርክ እንደምትለው፣ የጋራ ቤቶች ከአምስት ሰዎች በላይ አንድ ላይ የሚኖሩባቸው ናቸው።
“የተለየ የሚያደርገው በሰዎች መካከል ያለው ወጪን የመጋራት ፍላጎት ነው” ስትል ታብራራለች።
ከኑሮ ውድነት በተጨማሪ የቤተሰብ አባላት ተራርቀው መኖራቸው ለዚህ ዓይነት አኗኗር ምክንያት ሆኗል።
“ጥሩ ሕይወት ጥሩ ቤትን ያማከለ ነው ተብሎ ይታመናል። አብሮ መኖር ቀላል አይደለም። ሁሉም የራሱ ቤት እንዲኖረው ይመኛል” ትላለች።
ሆኖም ግን በጊዜያዊነትም ቢሆን ከደባሎች ጋር አብሮ የመኖር አማራጭን የሚከተሉ ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል።












