ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ናይጄሪያ በአንድ ግለሰብ ግድያ ምክንያት 2 ሺህ ሞተር ሳይክሎችን አወደመች
በናይጄሪያ ትልቁ ከተማ ሌጎስ ‘አካዳስ’ በመባል በሚታወቁት ተሽከርካሪዎች ላይ እገዳ መጣሉን ተከትሎ ከ2 ሺህ በላይ የተወረሱ ሞተር ሳይክሎች እንዲወድሙ ተደረገ።
እርምጃው የተወሰደው ባለፈው ወር አንድ ግለሰብ በተጠረጠሩ የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች መገደሉን ተከትሎ ሲሆን ይህም ቁጣን ቀስቅሷል።
የ38 ዓመቱ የድምጽ መሃንዲስ ሰንደይ ዴቪድ የተገደለው በሌኪ አቅራቢያ በሚገኝ የገበያ ቦታ በታሪፍ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ነበር።
ግድያው ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ይህም ባለሥልጣናት እርምጃ እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል።
የሟች ባለቤት ግሬስ ቦሉ፣ በባለቤቷ ግድያ ያዘነች ሲሆን ሁለት ልጆቿን እንዴት እንደምታሳድግ ተጨንቃለች።
“ እኔ የመንግሥት ሠራተኛ ነኝ። ሁሉንም ነገር የሚያደርገው ባለቤቴ ነበር። አሁን እኔ ይህንን እንዴት ማድረግ እችላለሁ ? የልጆቼን የትምህርት ክፍያ እና የቤት ኪራይ ለመክፈልስ ደመወዜ በቂ ነው ወይ?” ስትል የወደቀባትን መከራ ለቢቢሲ ተናግራለች።
በሞተር ሳይክሎቹ ላይ የተጣለው እገዳ ከአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ግብረ መልሶችን እያስተናገደ ነው። አንዳንዶች የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች የሚያሽከረክሩት በአደገኛ ሁኔታ ነው ሲሉ እርምጃው ተገቢ መሆኑን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ለወጣቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ እገዳውን ተቃውመውታል።
በኢኬጃ ነዋሪ የሆነው አንድ የእጅ ጥበበኛ ስለአሽከርካሪዎቹ አደገኛነት ይናገራል።
“የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ሰዎችን ያግታሉ። መንግሥት በእነርሱ ላይ የወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው። በሌጎስ ግዛት ችግር አንፈልግም። የትራንስፖርት ጉድለቱን ለመሙላት ተጨማሪ አውቶብሶች ይመደቡ” ሲልም አስተያየቱን ሰጥቷል።
እራሱን ፓስተር ነኝ ሲል የሚገልጸው አብረሃም የተባለ ነዋሪ ደግሞ ሞተር ሳይክል ማሽከርከር ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን በመግለጽ ምህረት እንዲደረግላቸው ጠይቋል።
“ በአገሪቷ ውስጥ ድህነት አለ። ሙሉ በሙሉ እነርሱን ማገድ ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አይደለም” የሚለው አብርሃም፣ አንዳንዶች ራሳቸውን ለመመገብ የሚሰማሩበት ሥራ እንደሆነና መንግሥት ይህንን ልብ ሊለው እንደሚገባ ተናግሯል።
እገዳው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ አንስቶ በተለምዶ ‘ኦካዳ’ የሚባሉት ሞተር ሳይክሎች የሚተራመሱበት የከተማዋ ክፍሎች ከወትሮው በተለየ ጸጥታ ሰፍኖባቸዋል።
እገዳው በኢቲ ኦሳ፣ ኢኬጃ፣ ሱሩልሬ፣ ሎጎስ ደሴት፣ ሌጎስ እና አፓፓ የተባሉ ስድስት አካባቢዎች ላይ የተጣለ ሲሆን ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከሦስት ቀናት በፊት ነው።
ባለፈው ወር እገዳው መጣሉን ያስታወቁት የሌጎስ ገዥ ባባጂዴ ሳንዎ ኦሉ፣ እገዳው በሞተር ሳይክሎቹ ሳቢያ የሚከሰት አደጋን እንደሚገታ ተናግረዋል።
ሞተር ሳይክሎች የትራፊክ መጨናነቅን በመፍጠር እና አደጋ በማድረስ ይታወቃሉ።
እንደ መንግሥት መረጃ ከሆነ እአአ ከ2016 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ውስጥ ብቻ በሌጎስ ግዛት ሞተር ሳይክሎች 10 ሺህ አደጋዎችን ያደረሱ ሲሆን ከ600 በላይ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆነዋል። ይህ አሃዝ በሆስፒታል የተመዘገበ ብቻ ነው።
ባለፈው ዓመት በከተማዋ ከደረሱ 20 ሺህ 596 አደጋዎች መካከልም 4 ሺህ 428 የሚሆኑት ማለትም 20 በመቶውን አደጋ ያደረሱት ሞተር ሳይክሎች ናቸው።
መንግሥት በሞተር ሳይክሎች ላይ እገዳ ሲጥል በሁለት ዓመት ውስጥ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
እአአ ከ1999 ጀምሮም ሁሉም የሌጎስ ገዥዎች በሞተር ሳይክሎች ላይ በከፊል አሊያም ሙሉ በሙሉ እገዳ ጥለዋል። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ አሽከርካሪዎች ሞተር ሳይክላቸውን ስለማያስመዘግቡ ሕግ ማስከበር አዳጋች ነው።
በዚህ ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብቻ 42 ሺህ የንግድ ሞተር ሳይክሎች መመዝገባቸውን የፌደራል መንገድ ደኅንነት ቢሮ አስታውቋል። በመሆኑም ሁሉንም ሞተር ሳይክሎች ከገበያው ማስወጣትም ቀላል አይሆንም።
አንዳንድ ሥራ የሌላቸው የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎችም ወደ ወንጀል ድርጊት ሊሰማሩ ይችላሉ የሚል ስጋትም አለ።
ይህ ብቻም ሳይሆን ሞተር ሳይክሎች በቀላሉ ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ ችሎታቸው፣ ፍጥነታቸው እና ምቹ ባልሆኑ መንገዶች መጓዝ በመቻላቸው የሕዝቡ በእነርሱ የመገልገል ፍላጎትም ከፍተኛ ነው።
በናይጄሪያ የሞተር ሳይክል ትራንስፖርት ማኅበር እገዳውን ተከትሎ በመንግሥት ላይ ክስ የመሠረተ ሲሆን ፍርድ ቤቱ መንግሥት ለአባላቶቹ አማራጭ የሥራ ዕድል እንዲሰጥና እገዳው ሕገ ወጥ መሆኑን እንዲገልጽ አሳስቧል።
የሌጎስ ግዛት ፖሊስ ቃል አቀባይ ቤንጃሚን ሁንደይን በበኩላቸው አሁን ላይ እገዳው ተግባራዊ የሚደረገው ለበጎ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፖሊስ ኮሚሽኑ እገዳውን ቀጣይነት ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚወሰዱ እርምጃዎችን ማውጣቱና ይህንን ለመከታተል አሠራር መዘርጋቱን ቃል አቀባዩ አክለዋል።
“በሞተር ሳይክል የሚሳፈር ማንኛውም ሰው በሕግ ይጠየቃል፣ ለዚህም በየቦታው የተቋቋሙ ተንቀሳቃሽ ፍርድ ቤቶች አሉ። እነዚህ ፍርድ ቤቶችም ቅጣቱን ይወስናሉ” ብለዋል።