ቶተነሃም ከሲቲ፤ መሪው አርሰናል በወራጅ ቀጠና ካለው ኤቨርተን ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎች ግምት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ21ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሁድ ቀጥሎ ይካሄዳሉ።
ሊጉ በዚህ ሳምንት ቶተነሃምን ከማንችስተር ሲቲ፣ የሊጉ መሪ የሆኑት መድፈኞቹ በወራጅ ቀጠና ካለው ኤቨርተን እንዲሁም ዩናይትድን ከፓላስ ያገናኛል።
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱቶን እንደተለመደው የዚህን ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።

ዓርብ
ቼልሲ ከ ፉልሃም

በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ አሸናፊው ፉልሃም ነበር። ቼልሲ በውሰት ያመጣው ጃኦ ፌሊክስ በመጀመሪያው ጨዋታ በቀይ ካርድ የተሰናበትበት ጨዋታ ነበር። ያን ጨዋታ ፉልሃም በደጋፊው ተደግፎ 2-1 አሸንፎ ነበር።
በዚህኛው ጨዋታስ? ቼልሲ በጥር የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ውድ ውድ ተጫዋቾቹን ወደ ሜዳ አስገብቶ በፉልሃም ላይ የበላይነትን ይይዝ ይሆን?
እንደ ሱቶን ከሆነ በቼልሲ ጉዳይ አሰልጠኝ ግራህም ፖተር እንኳ የክለባቸውን ምርጥ አሰላለፍ የትኛው ሊሆን እንደሚችል አያውቁም። በዚህም ምክንያት ይህን ጨዋታ መገመት አስቸጋሪ ይሆናል።
ግን ግን ፖተር በደጋፊያቸው ፊት ጨዋታውን አሸንፈው እፎይታ የሚያገኙ ይመስለኛል ይላል።
ግምት፡ ቼልሲ 2 -1 ፉልሃም።
ነገር ግን ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።
ቅዳሜ

ኤቨርተን ከ አርሰናል
የሊጉ መሪዎች መድፈኞቹ ቅዳሜ ከሰዓት በሚጀምረው ጨዋታቸው ጉዲሰን ፓርክ ላይ ኤቨርተንን ይገጥማሉ።
አርሰናል የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ማንሳት የሚያስችለውን ተጫዋቾች በጥር ወር አዘዋውረዋል ብዬ እገምታለሁ የሚለው ሱቶን፤ ኤቨርተን ደግሞ አንቶኒ ጎርደንን ለኒውካስል መሸጡ ትልቅ ኪሳራ ነው ይላል።
ኤቨርተን አንድም ተጫዋች ባያስፈርምም አዲሱ አሰልጣን ሾን ዳይሽ ቡድኑን ከመውረድ ለመታደግ የታቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ የሱቶን እምነት ነው።
ይሁን እንጂ ሾን ዳይሽ የኤቨርተን አሰልጣኝነት ግዜያቸውን የሚጀምሩት በሽንፈት ይሆናል ይላል።
ግምት፡ ኤቨርተን 0 - 2 አርሰናል

አስተን ቪላ ከ ሌስተር
ከዓለም ዋንጫ ወዲህ ሌስተር የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታን አላሸነፈም። በተቃራኒው ቪላ በኡናይ ኤምሪ እየተመሩ ጥሩ እየተጫወቱ ይገኛሉ።
ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስት ጨዋታዎች አሸንፈው በአንዱ አቻ ተለያይተዋል።
ጄምስ ማዲሰን ወደ ሜዳ መመለሱ ለሌስተር ለውጥ ይፈጥራል ይላል ሱቶን።
ግምት፡ አስተን ቪላ 1 - 1 ሌስተር

ብሬንትፎርድ ከ ሳውዝሃምተን
ሳውዝሃምተን ጥሩ እየተጫወተ ቢሆንም ድል ግን እየቀናው አይደለም። በሁሉም ውድድሮች ከባለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን ተሸንፈዋል።
ብሬንትፎርድ በሊጉ ከተሸነፈ ሦስት ወራት አልፈዋል። በሜዳቸው ደግሞ ከባድ ናቸው። ይህን ጭዋታ እንደሚያሸንፉ ይሰማኛል ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ብሬንትፎርድ 2 - 1 ሳውዝሃምተን

ብራይተን ከ በርንዝማውዝ
በርንዝማውዝ ወደ ብራይተን ሜዳ ተጉዘው ነጥብ ይዘው የሚመለሱበት ሁኔታ በጭራሽ አይታየኝም ይላል ሱቶን።
በሮቤርቶ ዲ ዜርቢ የሚመሩትን ብራይተን ጨዋታ መመልከት አስደሳች ነው ይላል ሱቶን።
ግምት፡ ብራይተን 3 - 0 በርንዝማውዝ

ማንችስተር ዩናይትድ ከ ክርስታል ፓላስ
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በነበረው የፓላስ እና የዩናይትድ ጨዋታ በባከነ ሰዓት ኦሊሴ ከቅጣት ምት ያስቆጠራት ጎል ዩናይትድን ወሳኝ ሦስት ነጥብን ያሳጣች ነበር።
ዩናይትድ ይህን ለመበቀል ኦልትራፎርድ ላይ ፓላስን ይጠብቃል።
ዩናይትድ በተለይ በሜዳው ድንቅ አቋም ላይ ይገኛል። ቀያይ ሴጣኖቹ በሜዳቸው ያለፉትን 12 ጨዋታዎችን አሸንፈዋል።
ያለ ዊልፍሬድ ዛሃ ወደ ሜዳ የሚገቡት ፓላሶች ፈተና ይጠብቃቸዋል።
ግምት፡ ማንችስተር ዩናይትድ 2 - 0 ክርስታል ፓላስ

ዎልቭስ ከ ሊቨርፑል
የሊቨርፑል አሰልጣኝ ጀርገን ክሎፕ ከአሁን በኋላ ሽንፈት ማስተናገድ የሚችል ትከሻ ያላቸው አይመስለኝም። ይሁን እንጂ ሊቨርፑል ከአስቀያሚው አቋማቸው ይላቀቃሉ ብዬ አላስብም ይላል ሱቶን።
በመከላከል ላይ ተሞርክዘው በመጫወት ጎላቸውን ላያስደፍሩ ይችላሉ። ዎልስ በዚህ የውድድር ዘመን እያሳዩ እንዳሉት በዚህ ጨዋታም ይህ ነው የሚባል የማሸነፍ ስሜት እና ጎል የማስቆጠር ብቃት ይኖራቸዋል ብዬ አላስብም።
ግምት፡ ዎልቭስ 1 - 1 ሊቨርፑል


ኒውካስል ከ ዌስት ሃም
ዌስት ሃም ከደካማ አቋም በኋላ ኤቨርተንን በማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ወጥተዋል።
ሱቶን ዌስት ሃሞች ሦስተኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት እና ድንቅ ከሆኑት ኒውካስሎች ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ተሸናፊ እንደሚሆኑ ጥርጣሬ የለኝም ይላል።
ግምት፡ ኒውካስል 1 - 0 ዌስት ሃም
እሁድ
ኖቲንግሃም ፎረስ ከ ሊድስ ዩናይትድ
ኖቲንግሃም ፎረስቶች ተጫዋች ማስፈረም ቀጥለዋል። ጋናዊውን አንድሪ አዬው 29ኛው ፈራሚያቸው ሆኗል። አሰልጣን ስቲቭ ኩፐር አዲስ ቡድን እያዋቀሩ አሁን ያሉበት ደረጃ ላይ ቡድኑን ማቆየት መቻላቸው ያስደንቃቸዋል።
ሊድስ ሦስት ነጥቦችን ከአንድ ጨዋታ ካገኙ ሰነባብተዋል። ይህ ጨዋታ በአቻ ይጠናቀቃል የሚል ግምtእ አለኝ።
ግምት፡ ኖቲንግሃም ፎረስ 2 - 2 ሊድስ ዩናይትድ

ቶተነሃም ከ ማንችስተር ሲቲ
የሳምንቱ ታላቁ ጨዋታ እሁድ ምሽት ቶተነሃምን ከሲቲ የሚያገናኘው ጨዋታ ነው።
ስፐርስ ይህን ማሸነፍ የሚችሉ ከሆነ ከሊጉ መሪዎች ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ከማስቻሉ በተጨማሪ ለሞራል ግንባታቸው ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።
ሶን በኤፍኤ ካፕ ፕሪስተን ላይ ጎል ማስቆጠሩ ወሳኙ ተጫዋች ወደጎል አዳኝነቱ ሊመለስ ይችላል የሚል ተስፋን ዘርቷል።
ይሁን እንጂ ሲቲ አሁንም ቢሆን የበላይነቱን እንደሚይዝ የሱቶን ግምት ነው።
ግምት፡ ቶተነሃም 1 - 3 ማንችስተር ሲቲ












