አንድ አውሮፕላን ምስጢራዊ ነው በተባለ ሁኔታ ባልቲክ ባህር ላይ ወደቀ

ታትሟል

ሴስና የተሰኘ የግል አውሮፕላን በላትቪያ የባህር ዳርቻ በባልቲክ ባህር ላይ ምስጢራዊ በሆነ ሁኔታ መከስከሱ ተገልጿል።

አውሮፕላኑ ከደቡባዊ ስፔን ከተነሳ በኋላ ከፍ እና ዝቅ እያለ የበረራ መስመሩን ሲስት የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ጄቶች ሊከታተሉት ሞክረዋል።

ባለስልጣናት አውሮፕላኑ አራት ሰዎችን አሳፍሮ እንደነበረ ይታመናል። በጀርመን ኮሎኝ ሊያርፍ ቢያቅድም አቅጣጫውን ቀይሮ ወደ ባልቲክ አቅንቷል።

የኔቶ አብራሪዎች እና የስዊድን ባለስልጣናት አውሮፕላኑን እየተከታተሉት የነበረ ቢሆንም በአብራሪዎች ክፍል ውስጥ ሰው ማየት አልቻሉም።

የላትቪያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ባወጠው መግለጫ "አውሮፕላኑ ከስፔን ወደ ኮሎኝ ይበር ነበር። አየር ላይ እያለ አውሮፕላኑ የበረራ መስመሩን ቀይሯል" ብሏል።

"የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ከአውሮፕላኑ ሠራተኞች ጋር መገናኘት አልቻሉም" ብሏል። ሴስና 551 ኦስትሪያ ውስጥ የተመዘገበ አውሮፕላን ነው። ባለቤቱ ግን ስፔን ውስጥ ነው።

የበረራ መረጃ የሚከታተለው ፍላይትራዳር24 አውሮፕላኑ ከስፔኗ ጄሬዝ ዴ ላ ፍሮንቴራ ከተማ መነሳቱን አስታውቋል።

ከተነሳ ከሰዓታት በኋላ ፍጥነት እና ከፍታውን መቀነሱን ድረ-ገጹ አስታውቋል።

የጀርመኑ ቢልድ ጋዜጣ በበኩሉ አውሮፕላኑ ከተነሳ በኋላ በአውሮፕላኑ ውስጥ ግፊት ችግሮች መፈጠራቸውን እና የአይቤሪያን ባሕረ ገብ መሬት ካለፈ በኋላ ግንኙነቱ እንደጠፋ ዘግቧል።

ከበርካታ ሃገሮች የተውጣጡ ተዋጊ ጄቶች አውሮፕላን በበረራው ወቅት ተከታትለውታል።

አውሮፕላኑ በላትቪያ ቬንትስፒልስ አቅራቢያ ባህር ውስጥ መውደቁ ከተዘገበ በኋላ የላትቪያ፣ የስዊድን እና የሊትዌኒያ የነፍስ አድን ቡድኖች በ​​አካባቢው ደርሰዋል።

አውሮፕላኑ የተከሰከሰው “ነዳጅ ስላለቀበት ነው” ሲሉ የስዊድን የነፍስ አድን ዘመቻ ኃላፊው ላርስ አንቶንሰን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል። አክለውም እስካሁን “የሰው አስከሬን አልተገኘም” ብለዋል።

አንቶንሰን እንደተናገሩት የነፍስ አድን ሠራተኞች ስለተፈጠረው ነገር “ምንም ማብራሪያ የላቸውም። ግምት መስጠት ብቻ ነው የምንችለው።” ብለዋል።