ጋዛ ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት የተመድ ሠራተኛ ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለወራት እስራኤል በተቀናጀ ጥቃት እየፈጸመችባት ባለችው ጋዛ በተፈጸመ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኛ ተገደሉ።
በትናንትናው ዕለት ግንቦት 5/ 2016 ዓ.ም የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች በደቡባዊቷ ጋዛ ራፋህ ከተማ ወደሚገኘው የአውሮፓ ሆስፒታል ጉዞ ላይ እያሉ በተፈጸመ ጥቃት አንድ የተቋሙ ሠራተኛ መገደሉ ይፋ ተደርጓል።
ከሟቹ በተጨማሪ ሌላ አንድ ግለሰብም በጥቃቱ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታውቋል።
ጥቃቱ ሲፈጸም ተጎጅዎቹ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተሽከርካሪ ተሳፍረው እየተጓዙ ነበር።
የመንግሥታቱ ድርጅት ጥቃቱ መፈጸሙን ይግለጽ እንጅ ጥቃቱን ያደረሰውን አካል ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል በጉዳዩ ላይ በሰጠው የመነሻ ማብራሪያ፣ “ጥቃቱ የተከሰተው በጦርነት ቀጠና ውስጥ ነው” ። ያለ ሲሆን፣ ተጎጅዎቹ ጉዞ ላይ እንደነበሩ እውቅና እንዳልነበረው ገልጿል።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል ክስተቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁለት አባሎቹ ላይ ጥቃት መፈጸሙን የሚገልጽ ሪፖርት እንዳቀረበለት አረጋግጧል።
ጉዳዩ በመጣራት ላይ መሆኑንም የእስራኤል የመከላከያ ኃይል አክሎ ገልጿል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ በድርጅታቸው ሠራተኛ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን መግለጻቸውን እና ለተጎጅ ቤተሰቦች መጸናናትን መመኘታቸውን የዋና ጸሐፊው ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
“ዋና ጸሐፊው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች ላይ የሚደርስን ማንኛውንም ጥቃት ያወገዙ ሲሆን፣ የተሟላ ምርመራ እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል” ብሏል መግለጫው።
በሌላ መግለጫ ዋና ጸሐፊው በሰጡት ማብራሪያ ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ እንስቶ እስካሁን ከ190 በላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራተኞች መገደላቸውን ገልጸዋል።
እስራኤል በከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ውስጥ የጀመረችውን የተቀናጀ ጥቃት ተከትሎ ከ35 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ስር ካለው የጤና ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ አመልክቷል።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1 ሺህ 200 ሰዎች መገደላቸውን እና 253 ታጋቾች መወሰዳቸውን የእስራኤል ባለሥልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።












